ኦባማ እና ባለቤታቸው ‘ወሳኝ ነው’ በተባለ እርምጃ ለካማላ ሃሪስ ድጋፋቸውን ሰጡ

ፋይል - የቀድሞ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ከምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ ጋር ስለ ተመጣጣኝ እንክብካቤ ህግ በዋይት ሀውስ በተዘጋጀ ሁነት ላይ ሲነጋገሩ ያሳያል፡፡ መጋቢት 27 ቀን 2014 ዓ.ም. (AP Photo/Carolyn Kaster, File)

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ እና የቀድሞዋ ቀዳማይ እመቤት ሚሼል ኦባማ፤ ካማላ ሃሪስ ቀጣይዋ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ለመሆን ለያዙት የምረጡኝ ዘመቻ የሚጠበቅ፤ ነገር ግን ወሳኝ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።

በዲሞክራት ፓርቲያቸው አባላት ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነት እና ተቀባይነት ያላቸው ኦባማ እና ባለቤታቸው ሚሼል በዛሬው ዕለት ለምክትል ፕሬዝዳንቷ የሰጡት ይህ ድጋፋቸው ይፋ የሆነው በጋራ ያደረጉት የስልክ ጥሪ በታየበት ቪዲዮ አማካኝነት ነው።

የድጋፍ ዜና የተሰማው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሪፐብሊካኑ እጩ እና የቀድሞ ተፎካካሪያቸው ትራምፕ ጋር ያደርጉት የነበረውን የዳግም ምርጫ ዘመቻቸውን በማቋረጥ፤ ድጋፋቸውን ለምክትል ፕሬዝዳንታቸው ሰጥተው መውጣታቸውን ተከትሎ፤ የፓርቲያቸው እጩ እንደሚሆኑ ለሚጠበቁት ሃሪስ የሚሰጠው ድጋፍ እየጎላ በመጣበት ባሁኑ ወቅት ነው።

በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ በመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዝዳንት እና በመጀመሪያዋ ጥቁር ቀዳማይ እመቤት፣ እና በምክትል ፕሬዝዳንትነት በማገልገል ባሉት የመጀመሪያዋ የእስያ እና የጥቁርያ ዝርያ ያላቸው ሴት መካከል ያለውን ወዳጅነት እና የተጋሩትን ታሪካዊ ገጽታ ምስል የሚያሳይ ይሆናል ተብሏል።

በቪዲዮ ምስሉም "ሚሼል እና እኔ የደወልነው ለሚያደርጉት የምርጫ ዘመቻ ያለንን ድጋፍ ስንሰጥ ያደረብንን ልባዊ ኩራት ለመግለጽ እና እርሶ በምርጫው አሸንፈው ወደ ዋይት ሃውስ እንዲገቡ የተቻለንን ሁሉ ለማድረግ መፈለጋችንን ለመግለጽ ነው" በማለት ኦባማ ለሃሪስ ሲናገሩ ይታያሉ።

“እህቴን ካማላን ‘ኮርቼብሻለሁ’ ሳልል ይህን ስልክ መደወል አልችልም” ያሉት ሚሼል ኦባማም በበኩላቸው "ታሪካዊ መሆኑም እሙን ነው" ብለዋል።