ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፣ 14ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሔድ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ሲገልጽ፣ የፓርቲው የቁጥጥር ኮሚሽን በአንጻሩ፣ ከጉባኤው ዝግጅት ራሱንና አባላቱን እንዳገለለ አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋራ ባደረጉት ውይይት፣ ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ከማካሔዱ በፊት፣ “በሕጋዊ መንገድ መመዝገብ እንዳለበት” አሳስበዋል፡፡
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት)፣ የፓርቲውን 14ኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሔድ አዘጋጅ ኮሚቴ አቋቁሞ እየሠራ እንዳለ፣ በማኅበራዊ የትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡
የህወሓት ቁጥጥር ኮሚሽን በበኩሉ፣ ትላንት ረቡዕ፣ ሐምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ለጠቅላላ ጉባኤው ዝግጅት፣ ካለፈው ሚያዝያ ወር ጀምሮ ሲሠራ እንደነበር አስታውሶ፣ ኢ- ዴሞክራሲያዊ አካሔድ እንደሚታይና ግልጽነት እየጎደለው እንደመጣ በመጥቀስ ተችቷል።
የጉባኤው ዓላማ፣ “በፓርቲው ውስጥ በተደራጁ ከፍተኛ አመራሮች ተጠልፏል፤” የሚለው የህወሓት ቁጥጥር ኮሚሽን፣ ይህም አባላቱ ከአዘጋጅ ኮሚቴው ራሳቸውን እንዲያገሉ ምክንያት መኾኑን ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።
ጠቅላላ ጉባኤው፣ “በፓርቲው ውስጥ መተማመንን በመፍጠር መካሔድ ይኖርበታል፤” ያለው ኮሚሽኑ፣ “ከዚኽ ውጭ የሚደረግ ጉባኤ በሚያስከትለው መዘዝ፣ የፓርቲው አመራር ሓላፊነቱን ይወስዳል፤” ሲል አሳስቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም፣ ባለፈው ሰኞ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችን በአገራዊ ጉዳይ ላይ ባወያዩበት ወቅት፣ ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤውን ከማካሔዱ አስቀድሞ፣ በተሻሻለው ሕግ መሠረት አስፈላጊውን ሰነድ አሟልቶ በምርጫ ቦርድ መመዝገብ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።
ህወሓት በበኩሉ፣ በፖለቲካዊ ውሳኔ የተሰረዘው የቀድሞ ሕጋዊ ሰውነቱ በፖሊቲካዊ ውሳኔ እንዲመለስለት እንጂ፣ እንደ ዐዲስ ፓርቲ መመዝገብ እንደማይፈልግ እየገለጸ ይገኛል፡፡
በጉዳዩ ላይ፣ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡት፣ የዓረና ለዴሞክራሲያዊ እና ሉዓላዊነት ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ዓምዶም ገብረሥላሴ፣ የህወሓት አመራሮች በግል ጥቅማቸው የሚፈጥሩት ልዩነት ሰፍቶ ወደ ግጭት እንዳያመራና ሕዝቡም ገፈት ቀማሽ እንዳይኾን ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል፡፡
አቶ ዓምዶም፣ ነገሮች በሰላም ብቻ ይጠናቀቁ ዘንድ፣ ኹሉም የኅብረተሰብ ክፍል ድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
“በፕሪቶሪያው ግጭት በዘላቂነት የማቆም የሰላም ስምምነት ላይ፣ ችግሮችን በፖለቲካ ውይይት ብቻ መፍታት እንደሚገባ ተቀምጧል፤” የሚሉት የሕግ ምሁሩ አቶ ሙስጠፋ ዓብዱ፣ “ኹሉም ነገር መታየት የሚገባው በዚኹ ስምምነት ዐይን ነው፤” ይላሉ፡፡
በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ እና በህወሓት የቁጥጥር ኮምሽን በፓርቲው ጉባኤ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች በተመለከተ፣ ከህወሓት ጽሕፈት ቤት መረጃ ለማግኘት በስልክ እና በአካል ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ህወሓት፣ ጠቅላላ ድርጅታዊ ጉባኤውን መቼ እንደሚያካሔድ በይፋ ያስታወቀው ቀን ባይኖርም፣ እስከ መጪው ሐምሌ 23 ቀን ድረስ፣ የጉባኤው ተሳታፊዎች እንደሚመረጡ ግን የወጣው መርሐ ግብር ያሳያል፡፡
ዝርዝሩን በድምጽ ለማድመጥ የተያያዘውን ፋይል ይከታተሉ።፡፡
Your browser doesn’t support HTML5