በሱዳን ለ15 ወራት የቆየውን አውዳሚ ጦርነት ለማቆም ተፋላሚ ወገኖች በመጪው ወር ስዊዘርላንድ ላይ ተገናኝተው የሠላም ንግግር እንዲያደርጉ አሜሪካ እና ሳዑዲ ዓረቢያ ጥሪ አድርገዋል።
ከተፋላሚ ወገኖቹ አንዱ የሆኑት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አዛዥ ጀኔራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ትላንት ማምሻውን ባወጡት መግለጫ፣ በአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስርት አንተኒ ብሊንከን የደረሳቸውን ጥሪ መቀበላቸውን አስታውቀዋል።
ሌላው ተፋላሚ የሱዳን ጦር ጠቅላይ አዛዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን በንግግሩ ላይ ይገኙ እንደሁ እስከ አሁን አላስታወቁም።
በፈረንጆቹ አቆጣጠር ነሐሴ 14 ሊጀመር የታቀደውን ንግግር ሳዑዲ ዓረቢያ በተባባሪነት እንደምታዘጋጅና፤ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ የግብፅ፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግስታት ተወካዮች በታዛቢነት እንደሚገኙ ብሊንከን ትላንት ባወጡት መግለጫ ላይ አስታውቀዋል።
“በሱዳን በመታየት ላይ ያለው ዕልቂት፣ ሰቆቃ እና ውድመት እጅግ አስከፊ ነው። ይህ ትርጉም የሌለው ጦርነት ሊያበቃ ይገባል” ብለዋል ብሊንከን በመግለጫቸው።
ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ባለፈው ሳምንት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የሱዳን ልዩ ልዑክ አደራዳሪነት ጀኔቫ ላይ በተወካዮቻቸው በኩል ተነገጋግረው ነበር። ልዩ ልዑኩ ራምታኔ ላማማር ውይይቱን “አበረታች” ሲሉ ገልጽውት ነበር።
ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ በሁለቱ ጀኔራሎች መካከል የተጀመረው ጦርነት በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ሲቀጥፍ፣ ከ10 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ሱዳናውያን ደግሞ ወደ ጎረቤት ሃገራት እንዲሸሹ አስገድዷል።