ትላንት በመላው ዓላም የተፈጠረውን የኮምፒውተር ሥርዓትና ቴክኖሎጂ መቋረጥ ተከትሎ፣ ዛሬ ቅዳሜ አየር መንገዶች፣ የንግድ ተቋማት እና የመንግስት ቢሮዎች ወደ ወትሮው እንቅስቃሴያቸው ለመመለስ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።
በችግሩ ዋና ተጠቂዎቹ የአየር መንገዶች እንደሆኑ ሲታወቅ፣ ትላንት በሺሕ የሚቆጠሩ በረራዎችን ለመሰረዝ ተገደዋል። አውሮፕላኖቻቸውና የበረራ ቡድናቸው መገኘት በሚገባቸው ቦታ ሳይገኙ ሲቀሩ፣ የአየር ማረፊያ ጣቢያዎች ደግሞ መንገደኞች መቀበያ እና መፈተሻ አገልግሎታቸው አሁንም እንደተመሳቀለ ነው።
በመላው ዓለም ለሚገኙ በርካታ ኩባንያዎች የሳይበር ደህንነት አገልግሎት በሚሰጠውና ክራውድስትራይክ በተሰኘው ኩባንያ፣ ማይክሮሶፍት ዊንዶውስ ለሚጠቀሙ ደንበኞች የተላከው ማሻሻያ (አፕዴት) በራሱ እክል የነበረው በመሆኑ ችግሩ ሊፈጠር ችሏል። የተፈጠረው ችግር የሳይበር ጥቃት ወይም ሌላ የደህንነት ችግር እንዳልሆነም ኩባንያው አስታውቋል።
በአውሮፓ የሚገኙ የአየር ማረፊያዎች ዛሬ ወደ ወትሮ አገልግሎታቸው የተመለሱ ሲመስሉ፣ የእንግሊዝ የመጓጓዣ አገልግሎት ወደ ወትሮው አሰራሩ ለመመለስ እየጣረ ነው ተብሏል።
ወደ አሜሪካበ በሰሜንና በደቡብ አቅጣጫ በየብስ የሚገቡ ተጓዦች በኬላዎች ላይ ለሰዓታት ለመጠበቅ ተገደው እንደነበር ታውቋል።