የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኅይሎች በዳርፉር የሚያካሂዱትን ጥቃት እንዲያቆሙ የጸጥታው ምክር ቤት ጠየቀ

  • ቪኦኤ ዜና

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በምስራቅ ናይል ግዛት፣ ሱዳን እአአ ሰኔ 22፣ 2019

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የምዕራባዊ ዳርፉር ዋና ከተማን ከበው የሚያካሂዱትን ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያቆሙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ትላንት ሐሙስ ባሳለፈው ውሳኔ ጠይቋል።

ሰፊ በሆነው የዳርፉር ምዕራባዊ አካባቢ እስካሁን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎቹ ያልተቆጣጠሯት ከተማ ኤል ፋሽር ብቻ ስትሆን፣ በውጊያው መካከል የተጠመዱት ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡት ነዋሪዎቿ መውጫ መንገድ አጥተዋል። ብሪታኒያ ያቀረበችው የውሳኔ ሃሳብ ሩስያ ድምጸ ተዓቅቦ ስታደርግ ካለ ተቃውሞ በ14 አባላት ድጋፍ አልፏል።

ውሳኔው በተጨማሪም ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እና የሱዳን የጦር ሠራዊት "ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው ጦርነት እንዲያከትም በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ላይ የሚደርሱበትን መንገድ እንዲፈልጉ" ሲል ጠይቋል።

ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው ጦርነት እንዲያከትም በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ላይ የሚደርሱበትን መንገድ እንዲፈልጉ"

ዳርፉር ውስጥ ሁከቱ እየተስፋፋ መሄዱ በእጅጉ እንደሚያሳስበው ያመለከተው የጸጥታ ምክር ቤቱ ውሳኔ፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች በሰሜን ዳርፉር ዋና ከተማ ኤል ፋሽር እና ባለፈው ዓመት ምዕራብ ዳርፉር ኤል ጂኒና ከተማ ውስጥ "ጎሣ ተኮር ጥቃት" መፈጸማቸውን የሚገልጹት ተዓማኒ ሪፖርቶች በጣም አሳሳቢ መሆናቸውን አመልክቷል።

ፈጥኖ ደራሽ ኅይሉ ተዋጊዎች እና የመንግሥቱ ኃይሎች የሲቪሎችን ደህንነት እንዲጠብቁ የሚጠይቀው ውሳኔ የኤል ፋሽር ነዋሪዎች ለቅቀው ለደህንነታቸው ወደተሻለ አካባቢ መሄድ መፍቀድ እንዳለባቸው አሳስቧል።

የተመድ የጸጥታ ምክር ቤት ውሳኔው አክሎም፣ በሱዳን በሚካሄደው ጦርነት የሰላም ጥረት ከማድረግ ይልቅ ጣልቃ ገብተው ጦርነቱን የሚያባብስ ሥራ የሚሠሩ ሀገሮች በሙሉ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠይቋል።

አስከትሎም ለተዋጊዎቹ ወገኖች የጦር መሣሪያ የሚሰጡ ሀገሮች የመንግሥታቱን ድርጅት የጦር መሣሪያ ማዕቀብ እየጣሱ በመሆናቸው ማዕቀብ ሊጣልባቸው እንደሚችል ማስታወስ እንደሚገባቸው ገልጿል።

በመንግሥታቱ ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ "የውጭ ጣልቃ ገብነቱ መቀጠል አስቀድሞም ያለውን አለመረጋጋት ከማባባስ ያለፈ ፋይዳ የለውም" በማለት አሳስበዋል።

አስከትለውም በሱዳን ያለው ሁኔታ እጅግ አደገኛ በሆነበት በዚህ ወቅት የተላለፈ ውሳኔ መሆኑን ያነሱት የዩናይትድ ስቴትሷ አምባሳደር " የኤል ፋሽር ሕዝብ በውጊያው ተጠምዷል። ከባድ መሣሪያ በታጠቁ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ተከቧል። ምግብ፥ መድሃኒት፥ እና ሌላውም መሠረታዊ አስፈላጊ ነገር እያለቀ የበረታ ቸነፈር እየመጣበት ነው። መጠነ ሰፊ የጅምላ ጭፍጨፋ ይፈጸማል የሚለው ስጋት እያየለ ነው" ብለዋል።