ቪኒሲየስን ዘረኛ ስድብ የሰደቡት በእስራት ተቀጡ

ፋይል፡ የሪያል ማድሪድ የእግር ኳስ ተጫዋች ቪኒሲየስ ጁኒየር

የሪያል ማድሪድ የእግር ኳስ ተጨዋቹን ቪኒሲየስ ጁኒየር ዘረኛ ስድብ ተሳድበዋል የተባሉ ሶስት የቫለንሲያ የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች ስምንት ወራት የእስር ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

ሶስቱ ተከሳሾች የተጨዋቹን የቆዳ ቀለም የሚመለከቱ ስድቦችን በጩኽት ማሰማታቸውን እና የእጅ ምልክቶችንም መጠቀማቸውን ያመለከተው ፍርድ ቤቱ፣ እነዚሁ ስድቦችና ምልክቶች ዘር ተኮር መሆናቸውን እንዲሁም ስድቦቹ በተደጋጋሚ የተሰሙና ተከሳሾቹ ባሳዩት የዝንጀሮ መሰል እንቅስቃሴ የተጨዋቹ ስሜት እንደተጎዳና ክብሩም እንደተነካ አስታውቋል።

ፍርዱ በስፔን ስቴዲየሞች ዘረኛ ስድብ ለሚያሰሙ ተመልካቾች የተሰጠ የመጀመሪያው ቅጣት ነው ተብሏል።
በስፔን ሕግ አሰራር ከሁለት ዓመታት ያነሰ ቅጣት የሚተላለፍባቸው ፍርደኞች፣ ቀደም ሲል ወንጀል ፈጽመው ካልሆነ በስተቀር ተፈጻሚ መሆኑ ያልተለመደ ሲሆን፣ በፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ የተባሉት ተከሳሾችም ሌላ ተጨማሪ ወንጀል ካልፈጸሙ በስተቀር ወደ ዘብ ጥያ ላይወርዱ ይችላሉ ተብሏል።

ጥፋተኝነታቸውን ያመኑት ተከሳሾች ለሁለት ዓመታት ወደ ስቴዲየም እንዳይገቡ የታገዱ ሲሆን፣ የፍርድ ሂደቱን ወጪም እንዲከፍሉ ታዘዋል።