እስራኤል በጋዛ በምታካሂደው መጠነ ሰፊ ጥቃት እየተባባሰ የሄደው ሰብዓዊ ቀውስ፣ ከሁለት አመት በላይ ያስቆጠረው የዩክሬን እና የሩሲያ ጦርነት ያስከተለው ውድመት፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በሱዳን የቀጠለውን ጦርነት ጨምሮ፣ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሚካሄዱ ግጭቶች፣ አደጋዎች፣ መፈናቀሎች እና ቀውሶች አብዛኛውን የዜና ሰዓት የሚሸፍኑ ዘገባዎች ናቸው።
እነዚህ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የተፈጥሮ አደጋ ቀውሶች በሰዎች ላይ የሚያስከትሉትን ስቃይ ጨምሮ የተለያዩ ውስብስብ እና አስቸጋሪ ርዕሰ ጉዳዮች እየተከታተሉ ለህዝብ የሚያደርሱት ደግሞ ጋዜጠኞች ናቸው።
በዚህ ምክንያት ጋዜጠኞች ለከፍተኛ ጭንቀት፣ ድብርት፣ የእንቅልፍ እና የአመጋገብ መዛባት እንዲሁም ድህረ አደጋ ውጥረት (PTSD) የተሰኘ የአዕምሮ ጭንቀት በሽታ እንደሚጋለጡ ጥናቶች ያመለክታሉ።
ካሳዬ ዳምጤ ላለፉት ስምንት አመታት በሰራችባቸው የተለያዩ ሚዲያዎች፣ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ወቅታዊ ግጭቶች እና የፖለቲካ አለመረጋጋቶች ያስከተሏቸውን ተፅእኖዎች እየተከታተለች ስትዘግብ የሚፈጥርባትን ስሜት ትገልጻለች።
ካሳዬ፣ በጥር ወር በአማራ ክልል፣ ሰሜን ጎጃም ዞን፣ መርዓዊ ከተማ በተፈፀመ ጥቃት ንፁሃን ዜጎች ሲገደሉ ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎችን እና የአይን እማኞችን አነጋግራለች። በሰሜን ሸዋ ዞን፣ የካቲት ወር ላይ፣ በአንድ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት በርካታ ሰዎች ሲገደሉም ተጎጂዎችን እና የአካባቢውን ነዋሪዎች አነጋግራ ዘገባውን አጋርታለች። ዘገባዎቹን ለሕዝብ ለማድረስ የሰበሰበቻቸው መረጃዎች ታዲያ ከፍተኛ የአይምሮ መረበሽ አስከትሎባታል ።
በትግራይ ቴሌቭዥን ውስጥ የምትሰራው አብሪሃ ካህሳይም በጋዜጠኝነት ሙያ 15 አመታትን አስቆጥራለች። ለሁለት አመት በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት በትግራይ ክልል ውስጥ የደረሰውን ውድመት በምትዘግብበት ወቅት ይደረሰባት የስነ-ልቦና ጉዳት ግን በቃላይ ሊገለፅ የማይችል ነው ትላለች።
ጋዜጠኞች በዓለም ላይ ያለማቋረጥ የሚከሰቱ አሳዛኝ እና አሰቃዊ ኹነቶች ወይም ታሪኮችን የሚዘግቡት ከሚዲያ ኢንዱስትሪው አቅም ማነስ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ የስራ ጫናዎችን፣ የደሞዝ ማነስ እና እርግጠኛ ያልሆነ የወደፊት እጣ ፈንታ ተቋቁመው ነው። ለምሳሌ አብርሃ ትግራይ ክልል ጦርነት ላይ በነበረበት ወቅት ደሞዝ አልነበራትም።
ጋዜጠኞች የሚዘግቧቸው ዜናዎች የሚያደርሱባቸው የስሜት ጫና በዘገባዎቻቸው ላይ እንዳይንፀባረቅ ጥንቃቄ ማድረግ የሙያው ስነምግባር ያስገድዳቸዋል። በመሆኑም ስሜታቸውን ከዘገባው ለማውጣት እና እና ሚዝናዊ በሆነ መንገድ ለህዝብ ለማድረስ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ይገልጻሉ። ለዚህም ሚዲያው ውስጥ በተዋረድ የሚያገለግሉ አዘጋጆች እና የአርትኦት ባለሙያዎች ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል።
በህክምና እና ስፖርት ዙሪያ ፅሁፎችን ዘገባዎችን በማጋራት የሚታወቀው የህክምና ባለሙያ እና የአይምሮ ጤና ተሟጋች ዶክተር ብሩክ ገነነ፣ እንደሚለው ጋዜጠኞች በስራቸው ምክንያት በተደጋጋሚ የሚሰሟቸው መልካም ያሆኑ ዜናዎች ከስራው ባህሪ ጋር ተዳምሮ የአይምሮ ጤናቸውን አደጋ ላይ ይጥለዋል።
ዶክተር ብሩክ በጋዜጠኝነት ስራው ምክንያት በጭንቀት እና በድባቴ የተጠቁ በርካታ ጋዜጠኞችን ያገኛል። በሚዘግቧቸው ዘገባዎች ምክንያት ስለማህበረሰቡ እና ስለዓለም ያላቸው አመለካከት ሲቀየርም አይቷል። በአይምሮ ጤናቸው ላይ የሚደርሰውን ጫና መቋቋም አቅቷቸው ስራቸውን የለቀቁ ወይም የቀየሩ በርካታ ጋዜጠኞችንም ያውቃል።
እሱ እንደሚለው ጋዜጠኞች በየእለቱ ከሚከታተሏቸው ከፍተኛ መጠን ያላቸው አሉታዊ መረጃዎች በተጨማሪ፣ በሚያጋሯቸው መረጃዎች ምክንያት በማህበራዊ መገናኛ እና በሌሎች መንገዶች የሚደርሱባቸው ጥቃቶችም ለተጨማሪ የአይምሮ ጤና ችግር ያጋልጧቸዋል።
በተለይ በማህበራዊ ትስስር ገጾች አማካኝነት ጋዜጠኞች የሚሰነዘሩ ጥቃቶች በማንነት ላይ ያነጣጠሩ መሆናቸውን የምትገልጸው ካሳዬም የጫናውን ክብደት ታስረዳለች።
ጋዜጠኞች በስራቸው ምክንያት በአይምሮ ጤናቸው ላይ የሚደርሰውን ችግር የበለጠ አዳጋች የሚያደርገው አብዛኞቹ የሚዲያ ተቋማት፣ በግንዛቤ እጥረት ወይም በአቅም ውሱንነት ምክንያት ችግሩን አውቀው ድጋፍ አለማድረጋቸው መሆኑን ባለሙያዎቹ ይስማሙበታል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ችግሩን እያስተዋሉ የመጡ የጋዜጠኞች ማህበራት ግን የተለያዩ ስልጠናዎችን በማዘጋጀት ግንዛቤ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ዶክተር ብሩክ ይገልጻል።
አብሪሃ የተመሳሳይ እንቅስቃሴ ተጠቃሚ ናት። የኢትዮጵያ የሴት ጋዜጤኞች ማህበር፣ በትግራይ ክልል አስከፊውን ጦርነት ይዘግቡ የነበሩ ጋዜጠኞች ከደረሰባቸው የአይምሮ ጠባሳ እንዲፈወሱ እና ስራቸውን መቀጠል እንዲችሉ የሰጠውን ስልጠና መውሰዷ ከስነ-ልቦና ጉዳት እንድታገግም እንደረዳት ትናገራለች።
ጋዜጠኞቹ ይህ አይነት የአይምሮ ጤና ድጋፍ እና ክትትል በሁሉም የሚዲያ ተቋማት መኖር አለበት ብለው ያምናሉ።
ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑ ጋዜጠኞች በስራቸው ምክንያት ለአይምሮ ጠባሳ ለሚዳርጉ ክስተቶች እንደሚጋለጡ ኒው ዮርክ የሚገኘው ኮሎምቢያ ዩንቨርስቲ ያቋቋመው ዳርት የተሰኘ የጋዜጠኞች ማዕከል ያካሄደው ጥናት ያመለከታል። በጋዜጠኝነት ትምህርት ቤቶች እና በዜና ክፍሎች ውስጥ ስለአይምሮ ጤና ትምህርት መስጠት፣ የአቻ ድጋፎችን ማመቻቸት እና እረፍት እንዲወስዱ ማበረታታት የሚዲያ ተቋማት እና ማህበራት ሊወሰዷቸው ከሚገቡ እርምጃዎች መካከል ጥቂቶቹ መሆናቸውም ተገልጿል።