የሩሲያ ባለስልጣናት ዩክሬን በሩሲያ ይዞታ ስር የምትገኘው ክሬሚያ ደቡባዊ ስፍራ በሚገኝ አንድ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ላይ በወሰደችውና ከ60 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በተጠቀመችበት ከባድ የሚባል ወታደራዊ ተልዕኮ ምክንያት፤ የነዳጅ ማጣሪያው ስራውን ለማቆም መገደዱን ዛሬ ጠዋት አስታውቀዋል።
የሩሲያ አየር መቃወሚያዎች በክራይሚያ ዘጠኝ አሜሪካ ሰራሽ ኤ.ቲ.ኤ.ሲ.ኤም.ኤስ ሚሳኤሎችን ከ 57 ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጋር፤ እንዲሁም በሩሲያ ክራስኖዳር ክልል እና በቤልጎሮድ ክልል ላይ ደግሞ ሦስት ሰው አልባ አውሮፕላኖች መምታቻቸውን፤ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አክሎ አስታውቋል።
በተያያዘ የስላቭያንስክ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ በስድስት ድሮኖች መመታቱን የአካባቢው ባለስልጣናት አረጋግጠዋል። ጥቃት የደረሰበት የስላቭያንስክ ማጣሪያ ፋብሪካ በዓመት 4 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዘይት የማጣራት አቅም ያለው ሲሆን በቀን 1 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ዘይት የሚመረትበት የነዳጅ ፋብሪካ ነው።
በጉዳዩ ላይ እስካሁን ድረስ ከኪየቭ ምንም አስተያየት አልተሰማም። ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬን የምዕራባውያን የጦር መሳሪያ መጠቀሟን የምትቀጥል ከሆነ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ሩሲያ ከመሰል ጥቃቶች እራሷን ለመከላከል እስካሁን ድረስ ጦርነቱ እንዳይባባስ እያከበረችው ካለው የጥንቃቄ መስመር ልታልፍ ትችላለች በማለት ያስጠነቀቁ ሲሆን፤ ይህም በሩሲያ እና በምዕራቡ መካከል ሰፊ ጦርነት ሊያስከትል ይችላል ብለዋል ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬን ሃይሎች ሩሲያ በአንድ ጀምበር ያስወነጨፈቻቸውን 37 ድሮኖች በሙሉ ማውደማቸውን የዩክሬን አየር ኃይል ሃላፊ እሁድ እለት ተናግረዋል።