የጋዛ ሆስፒታል እስራኤል በኑሰሪያት በፈጸመች ጥቃት 20 ሰዎች ሞቱ ሲል አስታወቀ

የእስራኤል ጥቃት በጋዛ ሰርጥ ግንቦት 11/2016

የእስራኤል ጥቃት በጋዛ ሰርጥ ግንቦት 11/2016

አንድ የጋዛ ሆስፒታል ዛሬ ዕሁድ እንዳስታወቀው በፍልስጤም ግዛት መሃል በሚገኘው የስደተኞች መጠለያ በሆነ መኖሪያ ቤት ላይ ባነጣጠረ የእስራኤል የአየር ጥቃት በትንሹ 20 ሰዎች መሞታቸውን ገልጿል።

"በማዕከላዊ ጋዛ ውስጥ በአል-ኑሴይራት የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ በሚገኘው ሀሰን የተሰኙ ግለሰብ ንብረት ላይ የእስራኤል የአየር ጥቃት ካደረሰ በኋላ፤ 20 ሰዎች ለሞት ሲዳረጉ በርካቶች ቆስለዋል" ሲል የአል-አቅሳ ሰማዕታት ሆስፒታል በመግለጫው አስፍሯል።

የዓይን እማኞች ጥቃቱ የተደረሰው በሀገሪቱ የሰዓት አቆጣጠር ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት መሆኑን የገለጹ ሲሆን የእስራኤል ሰራዊት ሪፖርቱን በማጣራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል። የዓይን እማኞች አክለውም በራፋ በሌሊት በተደረጉ የአየር ድብደባዎች ሌሎች በርካታ ቤቶች ዒላማ መደረጋቸውን የገለፁ ሲሆን በተወሰኑ ቦታዎች ላይ የአየር ድብደባ እና የመድፍ ድብበባዎች መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

የእስራኤል ጦር ከጥቃቱ ቀድም ብሎ በነበረው ቀን በጋዛ ተጨማሪ ሁለት ወታደሮቼ ተገድለዋል ብሏል። በጎሮጎርሳዊያን ጥቅምት 27/2023 የእስራኤል ጦር የእግረኛ ጦር ጥቃት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን በጋዛ ወታደራዊ ዘመቻ 282 ወታደሮች መሞታቸውን አስታውቋል።