በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን በቆንዳላ ወረዳ ባሉ ቀበሌዎች፣ ካለፈው ሳምንት ዐርብ ጀምሮ፣ በፌዴራል መንግሥት ኀይሎች እና በኦሮሞ ነጻነት ታጣቂዎች መሀከል በቀጠለው ውጊያ፣ የሰላማዊ ዜጎች ሕይወት ማለፉንና ለእንግልት የተዳረጉም መኖራቸውን፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል።
ስለ ኹኔታው ለአሜሪካ ድምፅ ያስረዱ ስማቸው በይፋ እንዳይገለጽ የጠየቁ የወረዳው ነዋሪ፣ አንድ የአሥራ አንደኛ ክፍል ተማሪ በቀበሌው ጽሕፈት ቤት አጠገብ ቆሞ ባለበት በመንግሥት ኀይሎች ከተያዘ በኋላ መገደሉን ተናግረዋል።
ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሌላው የአካባቢው ነዋሪም፣ በወረዳው ጊሚ ጋባ ቀበሌ ልዩ ስሙ ካዚ በተባለ አካባቢ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር አቶ ማሐሙዲ ታኖ፣ በቤጊ ወረዳ ልዩ ስሙ ኀሙስ ገበያ በተባለ አካባቢ በመንግሥት ኀይሎች ከተገደሉ በኋላ ባለቤታቸውንና ልጆቻቸውን ይዘዋቸው እንደሔዱ አስረድተዋል።
ባለፈው ሳምንት እሑድ፣ በወረዳው ቃባቼ ዱሌ በተባለ ቦታ በዕድር ስብሰባ ላይ በነበሩ ነዋሪዎች ላይ፣ የኦሮሞ ነጻነት ጦር አባላት ናችሁ፤ በሚል ተኩስ ከፍተውባቸው መበታተናቸውን የተናገሩት ሌላው ነዋሪ፣ እስከ አሁን ወደ ቤታቸው ያልተመለሱ ነዋሪዎች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም፣ በጫት ንግድ የሚተዳደሩ ሰባት ወጣቶች ከተያዙ በኋላ፣ “የሸኔ አባላት ናችሁ” ተብለው እንደታሰሩ፣ የቆንዳላ ወረዳ ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
ጊዜው የእርሻ ጊዜ እንደኾነ ያስታወሱት ነዋሪዎቹ፣ የመንግሥት ኀይሎችም ኾኑ ታጣቂዎች፣ ሲቪሎች በሚኖሩበት አካባቢ ግጭት ከመፍጠር እንዲታቀቡ ተማፅነዋል፡፡
በነዋሪዎቹ ለቀረበው ቅሬታ ምላሽ ለማግኘት፣ ከቆንዳላ ወረዳ አስተዳደር ጀምሮ እስከ ኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የአስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ድረስ በየደረጃው ጥረት መደረጉን ያመለከተው የፀሐይ ዳምጠው ዘገባ አለመሳካቱን አመልክቷል።