በእስራኤል የአየርና ምድር ጥቃት 19 ሰዎች ተገደሉ

  • ቪኦኤ ዜና

የእስራኤል ጥቃት በፍልስጤማውያን ይዞታ (ፎቶ ሮይተርስ)

እስራኤል ሌሊቱን በአየርና በምድር በመደብደብ 19 ሰዎች ከገደለችና በርካቶችን ካቆሰለች በኋላ ታንኮችዋን ሰሜን ጋዛ ሰርጥ ወደ ምትገኘው ምስራቅ ጃባሊያ መላኳን የጋዛ ጤና ባለሥልጣናት ተናገሩ፡፡

ጃባሊያ በጋዛ ከሚገኙት ስምንቱ ታሪካዊ የስደተኞች መጠለያ ካምፖች ትልቁ ስትሆን ከ100,000 በላይ ሰዎች ይኖሩባታል፡፡ ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ ፍልስጤማውያን ሲሆኑ፣ ዛሬ እስራኤል ከተባለችው ግዛት፣ እኤአ በ1948 ዓ.ም ለእስራኤል መፈጠር ምክንያት በሆነው፣ በአረብ እና የእስራኤል ጦርነት ሳቢያ ከነበሩባቸው ከተሞች የተባረሩ ናቸው፡፡

ቅዳሜ ማምሻው ላይ የእስራኤል ጦር በሰጠው መግለጫ “በጃባሊያ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎቹ፣ ጋዛን የሚቆጣጠረው ሃማስ ወታደራዊ አቅም ዳግም እንዳያንሰራራ እየከለከሉት ነው” ብሏል።

የእስራኤል ወታደራዊ ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ "ባለፉት ሳምንታት ሃማስ በጃባሊያ ወታደራዊ አቅሙን ለማደስ ያደረገውን ሙከራ አውቀናል። እነዚያን ሙከራዎች ለማስወገድ እየሰራን ነው" ብለዋል።

“የእስራኤል ኃይሎች የጋዛ ከተማ በሆነችው ዜይቱን ወረዳ ባደረጉት ዘመቻ 30 የፍልስጤም ታጣቂዎችን ገድለዋል” ሲሉ ሃጋሪ አክለዋል፡፡

ሰኢድ የተባሉ የ45 ዓመት የጃባሊያ ነዋሪ “ከትናንት ጀምሮ በአየርና በምድር የሚወርደው የቦምብ ድብደባ አልቆመም፣ መኖሪያቸውን ላጡት ሰዎች እንደመጠለያ የሚያገለግሉ የትምህርት ቤቶች አካባቢዎችን ጨምሮ ሁሉንም ቦታ እየደበደቡ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

“አዲሱ ወረራ በርካታ ቤተሰቦች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ያስገድዳቸዋል “ሲሉም ሰኢድ አክለዋል፡፡

የእስራኤል ጦር ታንኮቹን አልዘይቱን እና አልሳብራ ወደ ተባሉ የጋዛ ከተሞች ልኳል፡፡ ነዋሪዎች በእነዚህ ከተሞች የሚገኙ ሰማይ ጠቀስ ህንጻዎችን ጨምሮ በርካታ መኖሪያ ቤቶች በቦምብ መደብደባቸውን ተናግረዋል፡፡

የእስራኤል ጦር እነዚህን አካባቢዎች ከወራት በፊት የተቆጣጠራቸው መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡

“የእስራኤል ታንኮች ወደ ዲር አል ባላህ ዘልቀው ባይገቡም በከተማዋ ዳርቻ የሚገኘውን አጥር በታንክ ደርምሰው በመግባታቸው ከሀማስ ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገዋል” ሲሉ ነዋሪዎችና የሃማስ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ትናንት ቅዳሜ ረፋዱ ላይ በዴር አልባላ ከተማ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ሁለት ዶክተሮችና አባት እና ልጅ የሆኑ ሁለት ሰዎች መገደላቸውን የጤና ባለሥልጣናት ተናግረዋል፡፡

የሃማስ ታጣቂው ክንፍ እና የእስላማዊ ጅሃድ ተዋጊዎች፣ የጸረ ታንክ ሮኬቶችና የሞርተር ቦምቦችን በመጠቀም፣ ራፋን ጨምሮ፣ ጋዛ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች በእስራኤል ኃይሎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተናግረዋል፡፡