አፍሪካ የጤና ባለሙያዎች እጥረት እንዳለባት የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ። ድርጅቱ ይህን ያለው በናሚቢያ ዋና ከተማ፣ ዊንድሆክ በዚህ ሳምንት እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ የጤና ባለሞያዎች ፎረም ላይ ነው።
በፎረሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የናሚቢያ የጤና እና የማህበራዊ አገልግሎት ሚኒስትር ካሉምቢ ሻንጉላ፣ አፍሪካ ያጋጠማት የጤና ባለሙያዎች እጥረት አህጉሪቱ እ.አ.አ በ2030 ሁለንተናዊ የጤና ሽፋን ለማግኘት የያዘችውን እቅድ እንዳታሳካ እንቅፋት ይሆናል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
"የተሻለ ህይወት ፍለጋ አህጉሩን ጥለው የተሰደዱ አፍሪካውያን ቁጥር የሚስደነግጥ ነው" ያሉት ሻንጉላ፣ ይህን ጉዳይ የአፍሪካ መንግስታትም ሆኑ ታሪካዊ እና ወቅታዊ ሁኔታዎች ተለውጠው ማየት የሚሹ በሙሉ ቅድሚያ ሰጥተው ሊፈቱት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል።
የአፍሪካ በሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ዳይሬክተር ጀነራል ጂን ካሳያ እንዳስታወቁት፣ እ.አ.አ በ2030 ለመድረስ የታቀደውን ሁለንተናዊ የጤና ሽፋን ለማሳካት አፍሪካ ተጨማሪ 1.8 ሚሊየን የጤና ሰራተኞች ያስፈልጓታል።
በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ 1.55 የጤና ባለሙያዎች ለአንድ ሺህ ሰዎች አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን፣ ይህም ለ1ሺህ ሰዎች 4.55 የጤና ባለሙያዎች እንደሚያስፈልግ የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው ገደብ በታች ነው።
እ.አ.አ በ2023 ብቻ አፍሪካ 166 ወረርሽኞችን መመዝገቧን ያመለከቱት ካሳያ "የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት እ.አ.አ በ2030 ሁለት ሚሊየን የቋማዊ የማህበረሰብ የጤና ሠራተኞችን እንዲመለምሉ፣ እንዲያሰለጥኑ እና ወደ ስራ እንዲያሰማሩ የተወሰነውን ውሳኔ ለማሳካት በጣም ወደኃላ መቅረታቸውንም አመልክተዋል።