የራያ ወረዳዎች የግጭት ተፈናቃዮች ቁጥር 50 ሺሕ መድረሱን ኦቻ አስታወቀ

Your browser doesn’t support HTML5

የራያ ወረዳዎች የግጭት ተፈናቃዮች ቁጥር 50 ሺሕ መድረሱን ኦቻ አስታወቀ

በራያ አላማጣ፣ ዛታ እና ኦፍላ ወረዳዎች በተቀሰቀሰው የጸጥታ ችግር፣ ወደ ሰሜን ወሎ እና ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ዞኖች የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 50ሺሕ መድረሱን፣ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ በምኅጻሩ ዩኤን-ኦቻ አስታወቀ፡፡

ትላንት ሰኞ ባወጣው ሪፖርቱ፣ ተፈናቃዮቹ ያሉበትን አሳሳቢ ኹኔታ የጠቆመው ኦቻ፣ በተለይ ሴቶች እና ሕፃናት በሕይወት ለመቆየት ሰፊ ሰብአዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፤ ብሏል፡፡

ኹኔታውን ለማጥናት ወደ ስፍራው ግብረ ኀይል ልኮ እንደነበር የገለጸው የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በበኩሉ፣ ያገኛቸው በጣት የሚቆጠሩ ተፈናቃዮችን ብቻ እንደኾነ በመጥቀስ፣ ኦቻ ያወጣው ሪፖርት “የተጋነነና ከእውነት የራቀ ነው፤” ሲል አጣጥሎታል፡፡

ኮሚሽኑ ይህን ቢልም፣ የሰሜን ወሎ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ግን፣ በኦቻ የቀረበው ቁጥር ቢያንስ እንጅ አልተጋነነም፤ ብሏል፡፡ ኾኖም ከትላንት ጀምሮ፣ ተፈናቃዮቹን ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ሥራ በመሠራቱ፣ አሁን በቆቦ የቀሩት ተፈናቃዮች ቁጥር አነስተኛ እንደኾነ አስረድቷል፡፡

ኦቻ በሪፖርቱ፣ ከወልዲያ ከተማ ወደ ዋግ ኽምራ ዞን ሰቆጣ ከተማ ያለው መንገድ፣ የደኅንነት ስጋት ስላለበት በስፍራው ያለውን ተጨባጭ እውነታ ለመረዳት አለመቻሉን አመልክቷል፡፡

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት ደግሞ፣ ግብረ ሠናይ ድርጅቶቹ ስጋት ካለባቸው አማራጮችን በመፈተሽ ተፈናቃዮቹ የሚረዱበትን እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡