አሜሪካ፣ እንግሊዝና ፈረንሣይ ለዩክሬን በሚሰጡት ድጋፍ ምክንያት “ስትራቴጂካዊ አደጋ” የደቀነ እና የኑክሌር መሣሪያ ታጣቂ በሆኑት ኃያላን ሃገራት መካከልም መፋጠጥ እንዲኖር አድርጓል ሲሉ የሩሲያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ዛሬ ሰኞ ክስ አሰምተዋል።
ላቭሮቭ ጨምሮ እንዳሉት አሜሪካ እና የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)፣ በሩሲያ ላይ “ስትራቴጂካዊ ድል” ብለው የገለጹትን ለመፈጸም በመጓጓታቸው፣ ሁኔታው የኑክሌር አደጋ ስጋትን ደቅኗል ብለዋል።
“የምዕራቡ ዓለም ሃገራት፣ ከኑክሌር ታጣቂ ሃገራት ጋራ በቀጥታ ለመጋፈጥ በመሻት በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ፣ ይህም የሚያስከትለው ጉዳት አስከፊ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል ላቭሮቭ።
አሜሪካ እና አጋሮቿ በበኩላቸው፣ ዩክሬንን የሚረዱት ራሷን ከሩሲያ ወረራ እንደትከላከል መሆኑን በማሳወቅ፣ የኑክሌር ግጭት አደጋ እንደሚከተል በተደጋጋሚ በማስጠንቀቅ በምዕራቡ እና በምሥራቁ ዓለም መካከል ውጥረት እንዲሰፍን በማድረግ ላይ ያለችው ሩሲያ እንደሆነች በመግለጽ ላይ ናቸው።
አሜሪካ፣ እንግሊዝና ፈረንሣይ በምዕራቡ ዓለም ኑክሌር ታጣቂ ሃገራት ናቸው።