የሩሲያው ላቭሮቭ ስለዩክሬን ጦርነት ለመወያየት ወደ ቻይና ያቀናሉ

የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ

የሩሲያው የውጭ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ነገ ሰኞ እና ማክሰኞ በዩክሬንን ጦርነት ዙሪያ የሞስኮ እና የቤጂንግ ትብብርን ለማጠናከር በቻይና እንደሚቆዩ ታውቋል።

ሰርጌ ላቭሮቭ ‘ትኩስ ጉዳዮች’ ሲሉ የጠሯቸውን የዩክሬኑን እና የእስያ ፓስፊክ ቀውስ በተመለከተ እንዲሁም በጋራ ትብብሮች ዙሪያ ለመወያየት በቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ግብዣ ተደርጎልኛል ሲሉ ተናግረዋል።

ሮይተርስ ባለፈው ወር የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ወደ ቻይን በመጭው ግንቦት እንደሚጓዙ እና በዛም ከቻይና አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ጋር እንደሚገናኙ መዘገቡ የሚታወስ ነው። ቻይና ባለፈው የጎሮጎርሳዊያኑ ዓመት የዩክሬኑን ቀውስ ይቀርፋል ያለቸውን 12 ነጥቦች ያሉት ሰነድ ያዘጋጀች ሲሆን ሩሲያ የቻይና አቋም አመክኖያዊ ነው ስትል ምላሽ ሰጥታለች።

በሌላ በኩል ስዊዘርላንድ ጥር ወር ላይ የዩክሬኑ ፕሬዘዳንት ቮልደሚየር ዘለንስኪ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የሰላም ጉባዔ ለማዘጋጀት ፍቃደኛ ሆናለች። የሰላም ቀመሩን ቀደም ብለው ያስቀመጡት ፕሬዘዳንት ዘለንስኪ ሩሲያ አስቀድማ ከያዘቻቸው የዩክሬን ግዛቶች መልቀቅ ይኖርባታል ብለዋል።

ሞስኮ የዘለንስኪን ሀሳብ የማይረባ በማለት የወረፈችው ሲሆን በስዊዘርላንድ ተገናኝቶ መምከሩም ምዕራባዊያን ለዩክሬን ከሌላው ዓለም ድጋፍ የሚያሰባስቡበት ስልት ነው ስትል አጣጥላዋለች።