ከወራት አለመረጋጋት በኃላ ሴኔጋል ፕሬዚደንታዊ ምርጫ አከናወነች

ከወራት አለመረጋጋት በኃላ ሴኔጋል ፕሬዚደንታዊ ምርጫ አከናወነች።

ከወራት አለመረጋጋት በኃላ ሴኔጋል በከፍተኛ ፉክክር የታጀበ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በዛሬ ዕለት አድርጋለች ። በቅርብ ዓመታት ውስጥ በርካታ መፈንቅለ መንግስታትን ባስተናገደው ቀጠና የረጋ ዴሞክራሲ ባህልን ስለ ማስፈኗ የሚነገርላትን ምዕራብ አፍሪካዊት ሀገር መልካም ስም በቅርበ ወራት የታየው አለመረጋጋት ፈትኗል ።

የአሁኑ ምርጫ የተካሄደው ፕሬዚደንት ማኪ ሳል እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ምርጫውን ለማዘገየት ካደረጉት ያልተሳካ ጥረት ከሳምንታት በኃላ ነው ። ሳል በህገ መንግስቱ በተቀመጠው ገደብ መሰረት ለሶስተኛ ጊዜ እንዳይወዳደሩ ታግደዋል ።

የአሁኑ ምርጫ ሴኔጋል በ1960 ከፈረንሳይ ነጻነቷን ካገኘች ወዲህ የተደረገ አራተኛው ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ።

ቀደም ያለው የምርጫ ሂደት ግን በግጨት እና አለመረጋጋት የታወከ እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ለእስራት የተዳረጉበት ስለመሆኑም ተነግሯል ።

በአሁኑ ምርጫ ፉክክር በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ዕጩን ጨምሮ 19 ዕጩዎች ይወዳዳራሉ ። በሀገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ስለመሆኑ በተነገረለት በዚህ ምርጫ ከ50 በመቶ በላይ የህዝብ ድምጽ የሚያገኝ ዕጩ እንደማይኖር ተንታኞች ግምታቸውን አስቀምጠዋል ። በዚህም መሰረት የድጋሚ ምርጫ ይደረጋል የሚለው ግምት አይሏል ። ከዕጩ ተወዳዳሪዎች መካከል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አማዶ ባ እና ዕውቁ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ኦስማኒ ሶንኮ የሚደግፏቸው ባሲሮ ዲኦማዬ ይገኙበታል(AP)።