የዩናይትድ ስቴትስ ጦር አርብ እለት የየመን ሁቲዎች የሚጠቀሙበትን ሦስት የምድር ውስጥ ማከማቻ መምታቱን አስታወቀ። በኢራን የሚደገፉት አማፂያን በቀይ ባህር ላይ በሚጓዙ መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን እንደቀጠሉ ናቸው።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ባወጣው መግለጫ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ኃይሎች "በኢራን የሚደገፉ የሁቲ አሸባሪዎች ቁጥጥር ስር ባሉ የየመን አካባቢዎች የሚገኙ ሦስት የምድር ውስጥ ማከማቻ ስፍራዎች ላይ ራስን የመከላከል ዘመቻ ጥቃት" መፈፀሙን ገልጿል። በተጨማሪም አርብ እለት በተካሄደው ዘመቻ አራት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በተሳካ ሁኔታ ማውደሙን እና ሁቲዎች ወደ ቀይ ባህር የተኮሱትን አራት ፀረ-መርከብ ተወንጫፊ ሚሳይል መመከቱን አስታውቋል።
የሁቲ አማፂያን በጋዛ ለሚገኙ ፍልስጤማውያን አጋርነታቸውን ለማሳየት የእስራኤል፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካ ንብረት የሆኑት መርከቦችን እና ወደ እስራኤል ወደብ የሚያቀኑ መርከቦችን ዒላማ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
ጥቃቶቹ በቀይ ባህል ለሚጓዙ መርከቦች የሚደረገውን የመድህን ዋስትና ወጪ እንዲጨምር ያደረገ ሲሆን፣ በርካታ የመርከብ ኩባንያዎች መንገዳቸውን በመቀየር በደቡባዊ የአፍሪካ ክፍል ዙሪያ ጥምጥም ለመጓዝ ተገደዋል።