በትግራይ ክልል የተካሄደው ጦርነት አብቅቶ አሁን ሰላም ቢሰፍንም፣ ጦርነቱ ትቶት የሄደው ጠባሳ ከድርቅ እና የርዳታ አያያዝ ጉድለት ጋራ ተደማምሮ፣ በአንድ ወቅት ለምለም የነበረውን ሜዳ አሁን ምድረበዳ አድርጎታል። ፊታቸው በጭንቀት የተሞላ እናቶችም ልጆቻቸው በምግብ እጦት ሲዳከሙ እርዳታ በማጣት ይመለከታሉ። በትግራይ ክልል ደቡብ ምስራቅ ውስጥ የሚገኘው እና 13ሺህ ሰዎች የሚኖሩበት ፊናርዋ ከተማ፣ ረሃብ ከፀናባቸው አካባቢዎች አንዱ ሲሆን፣ በአካባቢው በሚኖሩ እናቶች እና ህፃናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው።
የጦርነት እና የድርቅ ጨካኝ እውነታዎች ለትንስኡ ህሉፍ ተደበላልቀውባታል። ትንስኡ የምትኖረው በኢትዮጵያ፣ ትግራይ ክልል፣ ደረቃማ አካባቢዎች ሲሆን፣ በቅርቡ በወሊድ ምክንያት የሞተች እህቷን አራት ልጆች ብቻዋን ታሳድጋለች።
በፌደራል ወታደሮች እና የክልሉ ታጣቂዎች መካከል ለሁለት ዓመት የተካሄደው ጦርነት አንዱን ልጇን ገድሎባታል። ሌሎቹ ራሳቸውን ችለው ቢኖሩም፣ በክልሉ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ከምታሳድጋቸው የእህቶቿ ልጆች ትንሹ ለምግብ እጥረት በሽታ ተዳርጓል።
"አክስታቸው እንደመሆኔ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ አራቱንም ልጆች እያሳደኩ ነው" የምትለው ትንስኡ "እርሻ የለም። ረሃብ እና በሽታ ብቻ ተስፋፍቷል። የምንፀዳዳበት ውሃ የለንም። ምግብ እጥረት አለ። ተስፋ መቁረጥ በረሃ ውስጥ ያገኘነውን እንድንበላ ያስገድደናል። በርካታ መኖሪያ ቤቶች በህመም እና በረሃብ ተጠቅተዋል" ስትል ያለውን ሁኔታ ታስረዳለች።
ትንስኡ ለተወሰነ ጊዜ በበረሃው ውስጥ ከሚታየው ቢጫ እና ድንጋያማ መልክዓ ምድር የወዳደቁ ፍሬዎችን እየለቀመች ለመመገብ ሞክራለች። አሁን ግን በቅርብ ወደሚገኘው ፊናርዋ ጤና ጣቢያ በመሄድ የአንድ አመት ህፃኗን ህይወት ለማትረፍ እየሞከረች ነው።
በጤና ማዕከሉ ውስጥ ግን ብቻዋን አይደለችም። ሌሎች እርዳታ የሚፈልጉ እናቶችም በዚህ 'ነባር ሀደንት' በተሰኘ የገጠር አስተዳደር ወደሚገኘው የጤና ማዕከል መጥተዋል። ከነዚህ አንዷ ከአስር ዓመት ልጇ ጋር ወደ ጤና ማዕከሉ የመጣችው አዳ አሬይ ግርማይ፣ በምግብ እጥረት የሚሰቃዩትን የአንድ ዓመት መንታ ልጆቿን፣ አሰፋ እና መተከልን፣ ለማሳከም እየተፍጨረጨረች ነው።
"በጤና ጣቢያው የምናገኘው ተጨማሪ ምግብ ልጆቼን አቆይቶልኛል። ብቸኛው የሚያገኙት የተመጣጠነ ምግብ እሱ ነው። በአንድ ወቅት ገበሬዎች ነበርን። አሁን ግን ምንም የለንም። ረሃብ ተስፋፍቷል። እነዚህ የአንድ አመት ህፃናት ያላቸው ተስፋ ይሄ ብቻ ነው" ትላለች አዳ አሬይ።
በፌደራል ምንግስት ደረጃ ከረሃብ ጋር የተያያዘ ሞት መኖሩን የሚገልፅ ሪፖርት ያልተለመደ ቢሆንም፣ ብሔራዊው እንባ ጠባቂ በጥር ወር ባወጣው ሪፖርት፣ ከጥር በፊት በነበሩት ስድስት ወራት ውስጥ 400 የሚጠጉ ሰዎች በትግራይ እና በአማራ ክልል በረሃብ መሞታቸውን አስታውቋል።
Your browser doesn’t support HTML5
ከነዚህ ውስጥ አብዛኛው ሞት የተመዘገበው ወደ 5.5 ሚሊየን ህዝብ በሚኖርባት ትግራይ ክልል ነው። ፊናርዋ ጤና ጣቢያ ወዲያው ለመመገብ ምቹ ሆነው የተዘጋጁትን አልሚ ምግቦች በመስጠት ህይወታቸው አደጋ ላይ ያሉትን ህፃናት ነፍሳቸውን እንዲያቆዩ ይጥራል።
ይህን አስከፊ ሁኔታ በእየለቱ የሚጋፈጡት የጤና ጣቢያው ዳይሬክተር አቶ ታደሰ መሃሪ ናቸው። በጦርነቱ ምክንያት ሁመራ ከሚገኘው መኖሪያቸው የተፈናቀሉት አቶ ታደሰ፣ በመቀሌ ጥገኛ ሆነው ከተቀመጡ ከሦስት ዓመት በኃላ፣ በፊናርዋ የጤና ባለሙያ ሆነው ማገልገል የሚችሉበት እድል አገኙ። አሁን በአካባቢው ያለውን አስከፊ ረሃብ ሲገልፁ "ምንም የሚበላ ነገር የለም። ምግብ ለማግኘት እና ህይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ፣ ከዚህ እርቀው ወደ የትኛውም አካባቢ ይሰደዳል። አሁን በዚህ አካባቢ በጣም ብዙ ሰዎች እየተሰቃዩ ነው። ተርበዋል። እየሞቱ ነው" ይላሉ።
ጦርነቱ፣ መቀሌ የሚገኘውን እና መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የሚጥረውን አይደር ሆስፒታል ጨምሮ፣ በርካታ የጤና ተቋማትን በማፈራረሱ፣ ተግዳሮቶቹ ብዙ ናቸው።
እ.አ.አ በህዳር 2022 የሰላም ስምምነት እስኪፈረም ድረስ፣ በፌደራል ወታደሮች እና ለክልሉ ታማኝ በሆኑ ኃይሎች መካከል ደም አፋሳሽ ጦርነት ተካሂዷል። ግጭቱ ካበቃ ከወራት በኃላ ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ዩናይትድ ስቴትስ፣ ለሰብዓዊ እርዳታ የሚገባው እህል በመንግስት ለመዘረፉ መረጃ እንደደረሰው በመግለፅ እርዳታ አቋርጠው ነበር።
በአካባቢው በተከሰተው ድርቅ ምክንያትም ህብረተሰቡ በቂ ሰብል ማምረት አልቻለም። በመሰቦ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት የ70 ዓመቱ ገበሬ ሀይሌ ገብረክርስቶስ፣ ባልተለመደ ድርቅ የተጠቃውን ደረቅ መሬት ለማረስ ይሞክራሉ። በአንድ ወቅት ከብቶች ይግጡባቸው የነበሩት ለምለም ማሳዎች አሁን ተራቁተው ኦና ሆነዋል።
በ1980ዎቹ የነበረውን የረሃብ ወቅት አሁንም የሚያስታውሱት አቶ ሀይሌ "ምንም የለንም። ምንም ነገር! አንዳንድ ሰዎች ያላቸው ንብረት፣ ከብት ሸጠው ህይወታቸውን ለማቆየት እየሞከሩ ነው። ሦስት ጊዜ ዘርተን ምንም የሚሰበሰብ እህል የለም። የምንበላው ስናጣ ከብቶቻችን በመሸጥ ነው ህይወታችንን የምናቆየው" ይላሉ አማራጭ በማጣት ከእርሻ ወቅት ቀድመው ከመሬታቸው ጋር እየታገሉ።
በሰብል መጥፋት ምክንያት የትግራይ ባለስልጣናት፣ እ.አ.አ በ1984 እና 85 የተከሰተው እና በሰሜን ኢትዮጵያ በመቶ ሺዎች ያለቁበት አይነት ረሃብ ሊከሰት ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ወና ቤታቸውን ታቅፈው መቀመት ያቃታቸው የነባር ሀደንት ወረዳ ነዋሪዎችም ወደ ወረዳው አስተዳዳሪዎች በመሄድ ምሬታቸውን ለማሰማትም ይሞክራሉ። እነዚህን ቅሬታዎች ላለፉት አምስት አመታት ያዳመጡት ሀያል ገብረኪዳን ምላሽ በማጣት ሰዎቹን ያለምንም እርዳታ እንደሚመልሷቸው ይናገራሉ።
"በአንድ ወቅት ይህ ስፍራ በጦርነቱ ለተፈናቀሉትም ጭምር የተስፋ ምንጭ ነበር። ለሁሉም ሰው የሚበቃ ነገር ነበረን። አሁን እራሳችንን እንኳን መመገብ አንችልም። ጦርነቱ ሁሉን ነገር ወስዶታል። የቀረ ነገር የለም።"
የምግብ እጥረቱን ያባባሰው፣ ነዋሪዎቹ ለችግር ግዜ ያከማቹትን እህል፣ በጦርነቱ ወቅት ለትግራይ ታጋዮች ድጋፍ ለማድረግ መለገሳቸው ነው። አንዳንድ ገበሬዎች ደግሞ፣ የፌደራል መንግስት እና አጋሮቻቸው እህሎቻቸውን እና ከብቶቻቸውን በግዳጅ እንደወሰዱባቸው ይናገራሉ።
በዩናይትድ ስቴትስ ዩንቨርስቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት ኤድጋር ጊቱዋ "መንግስት ምግብን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሞበታል። ለትግራይ ክልል የተሰጠውን እርዳታ በማስቀረት በዓለም አቀፍ ሰብዓዊንት ድንጋጌ የተቀመጠውን ህግ ተላልፏል። ሰላማዊ ዜጎችን ለአደጋ የሚያጋልጡ የጦርነት ዘዴዎችን መጠቀም የተከለከለ ነው" በማለት፣ የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ ርዳታ ዘረፋን ህወሓትን ለማዳከም እንደ ጦር ስልት እንደተጠቀመበት ይገልጻሉ።
በትግራይ ክልል በዝናብ ወቅት ለ60 ቀናት ዝንብ ያገኙ የነበሩ አካባቢዎች፣ አሁን በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ዝናብ የሚያገኙት ለጥቂት ቀናት ብቻ ነው። ነገር ግን እንደ አቶ ሀይሌ ያሉ ገበሬዎች አሁንም ተስፋ ሳይቆርጡ ማረሳቸውን ቀጥለዋል።