በዩናይትድ ስቴትስ የሚመራው ጥምረት 15 የየመን አማፂያንን ድሮን ማክሸፉን አስታወቀ

  • ቪኦኤ ዜና
የመን

የመን

ዩናይትድ ስቴትስ እና አጋር ኃይሎች ቅዳሜ እለት፣ በኢራን የሚደገፉት የየመን አማፂያን በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረሰላጤ ላይ የተኮሷቸውን 15 የድሮን ጥቃቶች ተኩሰው ማክሸፋቸውን የአሜሪካ ጦር አስታውቋል።

ብዙም ሳይቆይ አማፂያኑ ባወጡት መግለጫም፣ በአሜሪካ የንግድ መርከብ ላይ ሚሳይሎችን በመተኮስ እና በቀይ ባህር እና የኤደን ባህረሰላጤ ላይ የሚገኙ የዩናይትድ ስቴትስ የጦር መረከቦች ላይ ድሮኖችን በማሰማራት ጥቃት ማድረሳቸውን ገልፀዋል።

ጥቃቱ የሁቲ አማፂያን፣ ለዓለም ንግድ ወሳኝ በሆነው ቀይባህር ላይ በሚጓዙ መርከቦች ላይ የድሮን እና የሚሳይል ጥቃት ዘመቻ ከጀመሩ ከህዳር ወር አንሶቶ ከአካሄዷቸው ጥቃቶች ትልቁ እንደሆነ ተገልጿል። ቡድኑ ጥቃቱን የሚያካሂደው፣ እስራኤል ከሐማስ ታጣቂዎች ጋር በጋዛ ሰርጥ እያደረገችው ባለው ጦርነት፣ ለፍስጤማውያን ድጋፋቸውን ለማሳየት መሆኑን አስታውቀዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ማዕከላዊ ዕዝ "መጠነ ሰፊ" ሲል የገለፀው የሁቲዎች ጥቃት ጎህ ሳይቀድ በኤደን ባህረ ሰላጤ አቅራቢያ መድረሱን ገልጿል። ዕዙ አክሎ ድሮኖቹ "በአካባቢው የንግድ መርከቦች፣ የአሜሪካ ባህር ኃይል እና በቀጠናው በሚንቀሳቀሱ ሌሎች መርከቦች" ላይ ስጋት መደቀናቸውን አመልክቶ ጥምር ኃይሎቹ እርምጃ የወሰዱት "የመርከብ ጉዞ ነፃነትን ለመጠበቅ እና ዓለም አቀፍ ውሃ ደህንነቱ የበለጠ አስተማማኝ እንዲሆን ለማድረግ ነው" ብሏል።

እ.አ.አ ከ2015 ጀምሮ፣ በሳዑዲ የሚመራ ጥምረት የሁቲ አማፂያንን ለማጥፋት ለዓመታት የቆየ የቦምብ ጥቃት ቢያካሂዱም፣ አማፂያኑ አሁንም የየመንን ዋና ከተማ ሰንዓ እና አብዛኛውን የቀይ ባህር ዳርቻ ይቆጣጠራሉ።