እስራኤል በደቡብ ጋዛ ራፋ ከተማ ባደረሰችው የአየር ድብድባ 11 ሰዎች ሲገደሉ ወደ 50 የሚሆኑት ደግሞ መቁሰላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ዛሬ ቅዳሜ አስታወቀ፡፡
ከቆሰሉት መካከል ህጻናት እና ወንዶችን ጨምሮ ቢያንስ አንድ የጤና ባለሙያው በግብጽ ድንበር አቅራቢያ ወደሚገኘው ወደ ኩዌት ሆስቲፓል ተወስደዋል፡፡
በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎች አስክሬን በሆስፒታል ግቢ ውስጥ እንዲቀመጥ መደረጉን አሶሴይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እስራኤል ራፋ ውስጥ ካለው ኢሚራቲ ሆስፒታል ውጭ የሚገኙ ድንኳኖችን ኢላማ በማድረግ 11 ሰዎችን ስትገድል ወደ 50 የሚጠጉትን አቁስላለች ብሏል፡፡
ከሟቾቹ መካከል በሆስፒታሉ ሥራ ላይ የነበሩ አንድ ነርስ እና የጤና ባለሙያው እንደሚገኙበት ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
በጋዛ ሰርጥ አምስተኛ ወሩን ባስቆጠረው ጦርነት እስራኤል በየዕለቱ ከምታዘንበው የቦምብ ጥቃት በመሸሽ በራፋ የጋዛ ደቡባዊ ከተማ ራፋ የተጠለሉ 1.4 ሚሊዮን ፍልስጤማውያን ጉዳይ ከፍተኛ የሰአብዊ ቀውስ መፍጠሩን ዘገባው አመልክቷል፡፡