የእስራኤል ሃይሎች በጋዛ የመንግስታቱ ድርጅት የፍልስጤም ስደተኞች ረድኤት ተቋም ስር በመቶ ሜትሮች ርቀት ጥልቀት ያለው የሀማስ ወታደሮች ማዘዣ የሆነ ዋሻ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል። የእስራኤል ሰራዊት መሃንዲሶች በትላንትናው ዕለት ለአለም አቀፍ ጋዜጠኞችን ስፍራውን አስጎብኝተዋል። የውስጥ ለውስጥ ዋሻው 700 ሜትር ርዝመት እና 18 ሜትር ጥልቀት እንዳለው ተገልጿል።
ከዋሻው መገኘት በኋላ የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ የመንግስታቱ ድርጅት የፍልስጤም ተራድኦ ተቋም ዋና ኮሚሽነር ፊሊፔ ላዛሪኒ ስልጣናቸውን እንዲለቁ በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ማኅበራዊ ድረ ገጽ አውታር ላይ ጠይቀዋል።
ዋና ኮሚሽነር ላዛሪኒ ስለጉዳዩ “እብደት ብቻ ሳይሆን ይሄ ማስተዋል ማጣት ነው” በማለት ምላሽ የሰጡ ሲሆን ውጭ ጉዳይ እስራኤል ካትዝ ግን ምላሻቸውን አጣጥለዋል። የመንግስታቱ ድርጅት የፍልስጤም ስደተኞች ረድኤት ተቋም ባወጣው መግለጫ ላይ ተቋሙ ሀማስ እስራኤል ላይ የመጀመሪያውን የሽብር ጥቃት ከፈጸመ ከአምስት ቀናት በኋላ፤ ከጎርሳዊያኑ ጥቅምት 12 አንስቶ ከስፍራው ለቅቀው መውጣታቸውን በመግለጽ የእስራኤልን ግኝት “ለማረጋገጥም ሆነ አስተያየት ለመስጠት” እንደማይችል አስታውቋል።
ተቋሙ በተጨማሪም “የተ.መ.ድ የፍልስጤም ስደተኞች ረድኤት ተቋም የራሱ የደህንነትም ሆነ የወታደራዊ መከላከያ የለውም ስለዚህም በስፍራው ያለውን ሁኔታ ለመመርመር አቅም የለውም” ሲል አስፍሯል። ጉዳዩ በተ.መ.ድ ረድኤት ተቋማት ዘንድ ቀውስ ያስከተለ ሲሆን እስራኤል የተቋሙ አንዳንድ ሰራተኞ ለሀማስ ይሰራሉ በማለት ስትከስ የቆየች መቆየቷ ይታወሳል፤ ተቋሙ የራሱን ምርመራ ጀምሯል። አንዳንድ ለጋሽ ሀገራትም ለጊዜው የገንዘብ ድጋፋቸውን ማቆማቸውን አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል ፍልስጤማዊያን እስራኤል ከ13 ሺህ በላይ በጋዛ ሰርጥ ለሚገኙ ፍልስጤማዊያን የደም ስር ሆኖ የኖረውን የተ.መ.ድ የፍልስጤም ረድኤት ተቋም በሀሰት መረጃ ስሙን እያጠፋች ነው ሲሉ ከሰዋል። ተቋሙ በአካባቢው ላሉ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ክሊኒኮች እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ተደራሽ እንዲሁ ሲያደርግ ቆይቷል።
በተመሳሳይ ሀማስ በሲቪል ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች ውስጥ ይከለላል፤ የሚለውን ክስ ለረዥም ጊዜ ሲያስተባብል ቆይቷል። በአንጻሩ የእስራኤል ወታደራዊ ሀይል ዋሻው ትክክለኛ የሚገኝበት ቦታም እንዲገለጽም ሆነ ጋዜጠኞች ያለ ፈቃድ ፎቶ እንዲያሳዩ አለመፍቀዳቸው ተገልጿል።