ሪፐብሊካኖች የባይደን የማስታወስ ችሎታ ላይ ጥያቄ አነሱ

  • ቪኦኤ ዜና

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን (ፎቶ ኤኤፍፒ 02/08/24)

በአሜሪካ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት እና ፕሬዝደንታዊ እጩ ተወዳዳሪዎች የፕሬዝደንት ባይደንን ዕድሜና የማስታወስ ችሎታ በመጥቀስ አገሪቱን ለመምራት ብቁ አይደሉም ሲሉ ዘመቻ ከፍተዋል።

ባይደን የግብጹ አብደል ፋታህ ኤል-ሲሲን “የሜክሲኮው ፕሬዝደንት” ብለው በቅርቡ መጥራታቸውና፣ በቅርብ ሳምንታትም የዓለም መሪዎችን ስም እያሳሳቱ መጥራታቸው ለሪፐብሊካኖቹ የምርጫ ዘመቻ የተመቸ ሆኗል።

“ፕሬዝደምንቱ የሳለ አዕምሮ የላቸውም” ሲሉ የሪፐብሊካኑ ወገን በመሟገት ላይ ሲሆኑ፣ በምርጫ ዘመቻ ካሉት ኒኪ ሄሊ ቢሮ የወጣው መግለጫ ደግሞ፣ “ባይደን አገሪቱን በሚገባ ለመምራት የአዕምሮ ብቃት የላቸውም” ብሏል።

ምርጫው በሚከናወንበት በመጪው ህዳር “ባይደን የተሻለ የሰላ አዕምሮ ሊኖራቸው አይችልም” ሲሉ የቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ የምርጫ ዘመቻ አማካሪ ጄሰን ሚለር ተናግረዋል።

“የማስታወስ ቾሎታዬ መልካም ነው፣ ፕሬዝደንት ከሆንኩ ጀምሮ የሠራሁትን ተመልከቱ” ሲሉ ባይደን ምላሽ ሰጥተዋል።