“ሊብሮ” በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው አንጋፋው የስፖርት ጋዜጠኛ እና ታሪክ ዐዋቂ ገነነ መኩሪያ፣ በአደረበት ሕመም፣ ትላንት ሰኞ ምሽት ሕይወቱ ማለፉን፣ ቤተሰቦቹ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል፡፡ሥርዓተ ቀብሩም ነገ እንደሚፈፀም አስታውቀዋል።
የባለቤቱ ወንድም እንደኾኑ የገለጹልን አቶ ዮናስ አየለ፣ ገነነ የነበረበት የስኳር ሕመም ላለፉት ሦስት ወራት ጸንቶበት እንደቆየ ገልጸው፣ በ58 ዓመቱ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ሕይወቱ እንዳለፈ፣ ለአሜሪካ ድምፅ አስታወቀዋል፡፡
ስፖርትን ከታሪካዊ ወጎች ጋራ በሚያሰናኝበት ቀልብ ሳቢ አቀራረቡ የሚታወቀው ገነነ መኩሪያ ወይም ሊብሮ፣ ሀገራዊ ስፖርታዊ ክንውኖችን አስመልክቶ፣ በኅትመት እና የብሮድካስት ብዙኀን መገናኛዎች በሚሰጣቸው ትንታኔዎች ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር ፕሬዘዳንት ንዋይ ይመር፣ በስፖርት ጋዜጠኝነት ሞያው ከገነነ ጋራ ለረጅም ዓመታት የዘለቀ ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጾ፣ በእግር ኳስ ተጫዋችነት እና አሠልጣኝነት የዳበረ ልምዱን ለባለሞያዎች በለጋስነት የሚያካፍል የሥራ አጋር እንደነበረ ይመሰክራል፡፡
ገነነ፣ ስፖርታዊ ክንውኖችን አስመልክቶ፣ “ሊብሮ” በተሰኘው ጋዜጣው በሚያቀርባቸው ዘገባዎች እና መጣጥፎች አብዝቶ እንደሚታወቅ፣ ንዋይ ይመር አውስቷል፡፡ በኋላም ወደ ብሮድካስት ብዙኀን መገናኛ የተሸጋገረው ገነነ፣ ይሠራቸው የነበሩ በሰነድ ማስረጃዎች የዳበሩ ዘገባዎች እና ትንታኔዎች፣ በጎ ተጽእኖ መፍጠር እንደቻሉ ገልጿል፡፡
የስፖርት ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ፣ “ተንቀሳቃሽ ቤተ መጻሕፍት” በሚል የተወደሰበትንና በተለያዩ ዘርፎች ያካበተውን ጠቅላላ ዕውቀት እና መረጃ፣ ከአምስት በላይ በሚኾኑ መጻሕፍቱ ቀንብቦ ለትውልድ ለማስተላለፍ እንደበቃ ንዋይ ጠቅሷል፡፡
ገነነ፣ በስፖርቱ ዘርፍ ላበረከተው የዓመታት አስተዋፅኦም፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን(CAF)፣ በ2009 ዓ.ም. የ“ጎልደን ኦቭ ሜሪት” ሽልማት አበርክቶለታል፡፡
የሁለት ልጆች አባት የኾነውና ለአራት ዐሥርት ዓመታት በስፖርት ጋዜጠኛነት ሀገሩን በትጋት ያገለገለው የገነነ መኩሪያ ሥርዓተ ቀብር፣ ነገ ረቡዕ ከቀኑ በ9፡00፣ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም፣ ቤተሰቦቹ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል፡፡