ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ዛሬ የገና በዓልን እያከበሩ ነው። የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናትም ቅዳሜ ምሽት የተካሄዱ የገና ዋዜማ የፀሎት ሥነስርዓቶችን በታደሙ ምዕመናን ተጨናንቀው ነበር። ሆኖም በመላው ዓለም የነበረው የበዓሉ ድምቀት በግጭቶች የተጋረደ እንደነበርም ተገልጿል።
በዓለማችን ትልቁ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን አማኞች ቤተክርስቲያን በሆነው የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሪ የሆኑት ፓትሪያርክ ኪሪል ሞስኮ በሚገኘው የክርስቶስ ካቴድራል ተገኝተው ሰፋ ያለ እና ብዙዎች የታደሙበት የፀሎት ስነስርዓት መርተዋል። ያጌጡ ልብሶችን የለበሱ በደርዘን የሚጠጉ ቄሶች እና ካህናትም እጣን የሞላበት የወርቅ መዕጠንት ይዘው እና ልዩ የማህሌት ዜማ እያሰሙ ሥርዓተ ቅዳሴውን ታድመዋል።
የፀሎት ስርዓቱ ከመጀመሩ በፊት የገና በዓል መልዕክት ያስተላለፉት ፓትሪያርክ ክሪል፣ "እየሱስ ክርስቶስ ከተሳሳተ የህይወት ጎዳና፣ ከተሳሳተ የህይወት አቅጣጫ አድኖናል" በማለት ስለመስዋዕትነት ፍቅር ተናግረዋል። ምዕመኑ በሩሲያ "ምንም አይነት ክፋት ሰላማዊ ህይወትን እንዳያስተጓጉል" እንዲፀልዩም ጠይቀዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሞስኮ ምዕራባዊ ዳርቻ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ባደረጉት የገና ዋዜማ ዝግጅት ላይም፣ በዩክሬን ጦርነት ህይወታቸውን ያጡ ወታደሮች ቤተሰቦች ተገኝተዋል።
ፑቱን ለገና በዓል ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልክታቸው የሀይማኖት ተቋማት ጀግኖችን ለመደገፍ የሚያደርጉትን ጥረት አጉልተው አሳይተዋል።
በሌላ በኩል አብዛኛው ህዝቧ የኦርቶዶክስ ክርስትና ሀይማኖት ተከታይ በሆኑባት ዩክሬን፣ ሐምሌ ወር ላይ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ቮለድሚር ዘለንስኪ በፈረሙት ረቂቅ ህግ መሰረት፣ የገና በዓል እ.አ.አ በታህሳስ 25 እንዲከበር በመወሰኗ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ገና ዛሬ ሳይከበር ቀርቷል።
በጎረቤት በሚገኙ ቤላሩስ እና ሰርቢያ የሚገኙ የኦርቶዶክስ አማኞች ግን በአብያተ ክርስቲያናት እና ከቤተመቅደሶች ውጭ ባሉ አገልግሎቶች ላይ ልዩ መዓዛ ያላቸው የዛፍ ቅጠሎችን በማጨስ እና የቤተክርስቲያናት ሥርዓተ ቅዳሴን በመካፈል አክብረዋል። በግሪክ፣ አርሜኒያ፣ ኢራቅ አና በሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮችም እንዲሁ በዓሉን በተለያዩ ስነስርዓቶች አክብረዋል።