በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የጥላቻ ንግግር እያደገ መምጣቱን ገልጾ ተመድ አስጠነቀቀ

ፋይል - በኪንሻሳ በተካሄደ የተቃውሞ ሰልፍ፣ አንድ የፖሊስ አባል በተቃዋሚ ደጋፊዎች ላይ ድንጋይ ሲወረውር ይታያል - ታህሳስ 27፣ 2023

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተካሄደውን አጨቃጫቂ ምርጫ ተከትሎ፣ የጎሳ ግጭት እና የአመፅ ጥሪ እየተስፋፋ በመምጣቱ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ባለስልጣን እሁድ እለት ሁኔታው አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በታህሳስ ወር የተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ እና፣ የብሄራዊ እና የክልል ህግ አውጪዎችን ለመምረጥ የተካሄደው የአካባቢ ምርጫ፣ በአፈፃፀም መዘግየቶች እና በአሰራር ትርምሶች የተሞላ እንደነበር ተገልጿል።

ብሄራዊ የምርጫ ኮሚሽኑ እስካሁን የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ብቻ ይፋ ማድረግ የቻለ ሲሆን፣ ተቃዋሚዎች ውድቅ ባደረጉት በዚህ ምርጫ አሁን በስልጣን ላይ የሚገኙ ፊሊክስ ሺሴኬኪ ማሸነፋቸው ተገልጿል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮከር ተርክ "በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እየጨምረ የመጣው ብሔርን መሰረት ያደረጉ የጥላቻ ንግግሮች እና ለግጭት ማነሳሳት በጣም ያሳስበኛል" ያሉ ሲሆን በተለይ በሰሜን እና በደቡብ ኪቩ ምስራቃዊ ክልሎች፣ እንዲሁም በካሳይ እና ካታንጋ አካባቢዎች ያለው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ገልፀዋል።

ኪቩ ለበርካታ አስርት አመታት በታጠቁ ቡድኖች እና ብሔርን መሰረት ባደረጉ ጉድያዎች ሲሰቃይ የቆየ ነው።

"ጥላቻ የተሞላባቸው፣ የሰውን ክብር የሚጎድፉ እና ቀስቃሽ ትርክቶች አፀያፊ ናቸው" ያሉት ተርክ፣ በሀገሪቱ ያለውን ውጥረት እና ብጥብጥ እንደሚያባብስ አስጠንቅቀዋል።