ብሊንከን የግጭት መስፋፋት ስጋት ውስጥ የሚገኘውን መካከለኛው ምስራቅ ጎበኙ

  • ቪኦኤ ዜና
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ከዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አይማን ሳፋዲ ጋር በተገናኙበት ወቅት - ጥር 7፣ 2024

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ከዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አይማን ሳፋዲ ጋር በተገናኙበት ወቅት - ጥር 7፣ 2024


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን እሁድ እለት በዮርዳኖስ ተገኝተው ከንጉስ አብዱላህ ሁለተኛ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አይማን ሳፋዲ ጋር ተገናኝተዋል። በተጨማሪም ብሊንከን ወደ ጋዛ የሚጓዝ የእህል እርዳታ የጫኑ መኪናዎች የሚገኙበትን የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን ጎብኝተዋል።

ዮርዳኖስ፣ ብሊንከን፣ በእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት እየተናወጠ ባለው ቀጠና ውስጥ በሚያደርጉት ጉዞ ከጎበኟት ሀገር አንዷ ናት። ዮርዳኖስም ሆነ ሌሎች የአረብ ሀገራት በአስቸኳይ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲካሄድ ቢጠይቁም፣ እስራኤል ግን እስካሁን ጥሪውን አልተቀበለችም።

ብሊንከን፣ እስራኤል በጋዛ እየወሰደች ያለችውን እርምጃ ጠንካራ ተቺ ከሆኑት ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ረሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን እና ከግሪክ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪሪያኮስ ሚትሶታከስ ጋርም ተገናኝተው ተነጋግረዋል።

ብሊንከን ቅዳሜ እለት ለጋዜጠኞች ባደረጉት ንግግር፣ ቱርክ የጋዛ ግጭት ወደ ቀሪው የቀጠናው ክፍል እንዳይስፋፋ ለማድረግ በመካከለኛው ምስራቅ ያላትን ተፅእኖ ለመጠቀም ተዘጋጅታለች ብለዋል።

ብሊንከን በመካከለኛው ምስራቅ ዲፕሎማሲያው ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት፣ በጋዛ ያለውን ሁኔታ ለማረጋጋት እና በቀጠናው የተፈጠረውን ፍጥጫ ለማብረድ ነው።

ከብሊንከን ጋር የጎንዮሽ ስብሰባ ያደረጉት የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ሃካን ፊዳን በበኩላቸው በጋዛ "አስቸኳይ የተኩስ ማቆም እንዲደረግ" እና ያልተቋረጠ ሰብዓዊ እርዳታ ፍሰት እንዲጀመር ጠይቀዋል። በተጨማሪም ፊዳን፣ ሁለት መንግስት እንዲመሰረት በሚጠይቀው የመፍትሄ ሃሳብ ዙሪያ ድርድር እንዲጀመር ግፊት ማድረጋቸውን የቱርክ ዲፕሎማሲያዊ ምንጮች ገልፀዋል።