ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በጋዛ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅማለች የሚል ክስ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረበች ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ እስራኤል ጥቃቷን እንድታቆም ትእዛዝ እንዲሰጥ በትላንትናው ዕለት ጠይቃለች።
ደቡብ አፍሪካ ለዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ያቀረበችው ክስ “በእስራኤል የሚፈጸሙ ድርጊቶች እና ግድፈቶች... በባህሪያቸው የዘር ማጥፋት ወንጀል ናቸው” የሚል ሲሆን እስራኤል ቁርጠኛ የሆነ ዓላማ በመያዝ “በጋዛ ውስጥ የሚገኙ ፍልስጤማውያንን በማጥፋት በሰፊው የፍልስጤም ብሄራዊ፣ ዘር እና ጎሳ የማጥፋት እቅድ እየተገበረች ነው" ብላለች።
ክሱ በተጨማሪም ተቀማጭነቱ በሄግ የሆነውን ፍ/ቤት እስራኤል ጥቃቷን እንድታቆም የአስቸኳይ ጊዜያዊ ማዘዣ እንዲያወጣ ጠይቋል።
ደቡብ አፍሪካ እሷም ሆኑ እስራኤል የጉባኤው ፈራሚዎች በመሆናቸው ጉዳዩን በዘር ማጥፋት ኮንቬንሽን ስር ልትወስደው ትችላለች።