በእስራኤል እና በሐማስ ጦርነት ምክንያት በቤተልሔም ይካሄዱ የነበሩ የገና ክብረ በዓላት በመሰረዛቸው፣ በምዕመናን ይጨናነቅ የነበረው የእየሱስ ክርስቶስ የትውልድ ስፍራ በገና ዋዜማ ሰው አልባ ሆኖ አልፏል።
በየዓመቱ በዓሉን ለማክበር ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ይመጡ ከነበሩ ጎብኚዎች በተጨማሪ፣ በጎዳናዎች ላይ ይሰቀሉ የነበሩ መብራቶች እና የገና ዛፎችም በዘንድሮ የገና በዓል አይታዩም። በደርዘን የሚቆጠሩ የፍልስጤም ፀጥታ ኃይሎች ግን ጭር ያለውን ሜንጀር አደባባይ ሲጠብቁ ውለዋል።
ላለፉት ስድስት ዓመታት በእየሩሳሌም የኖረው ቬትናማዊ መነኩሴ ጆን ቪን፣ "በዚህ አመት፣ ያለ ገና ዛፍ እና የገና መብራቶች ጨለማ ውጦናል" ሲል ያለውን ስሜት አስረድቷል።
አፍቲም የተባለ ሬስቶራንት ባለቤት የሆነው አላ ሳላሜህ በበኩሉ "በጋዛ ሰዎች የሚገቡበት መኖሪያ ቤት እንኳን ሳይኖራቸው እኛ እንደ ተለመደው ዛፍ ማስጌጥና በዓል ማክበራችን ትርጉም የለውም" ሲል ተናግሯል።
ኾኖም በቤተልሔም የገና ክብረ በዓል መሰረዙ ለከተማው ኢኮኖሚ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል ተገልጿል። ቱሪዝም 70 ከመቶ የሚኾነውን የቤተልሔም ገቢ የሚሸፍን ሲሆን፣ አብዛኛው ገቢ የሚገኘው በገና ሰሞን ነው።
በርካታ የአየር መንገዶችም ወደ እስራኤል የሚያደርጉትን በረራ በመሰረዛቸው፣ በቤተልሔም ይንቀሳቀሱ የነበሩ ከ70 በላይ ሆቴሎች ለመዘጋት መገዳቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት አስታውቀዋል። በዚህም ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ስራ አጥ ሆነዋል።
በጋዛ የሚካሄደው ጦርነት ዌስት ባንክ ላይም ተፅእኖ ያሳደረ ሲሆን ቤተልሔም እና ሌሎች በእስራኤል ቁጥጥር ስር የሚገኙ የፍልስጤም ከተሞች ውስጥ ህይወት አስቸጋሪ ሆኗል።
በእስራኤል የተቀመጡ እገዳዎች እና ወታደራዊ ኬላዎች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ከግዛታቸው እንዳይወጡ እና እስራኤል ውስጥ መስራት እንዳይችልሉ አግዷቸዋል።