የአቶ ታየ ደንዳአ ባለቤት፣ ላለፉት አራት ዓመታት ከኖሩበት የመንግሥት ኪራይ ቤት፣ ዛሬ በጸጥታ ኃይሎች ለቀው እንዲወጡ መደረጋቸውን፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናገሩ።
ከመንግሥት የኪራይ ቤቶች አስተዳደር እንደመጡ የገለጿቸው ሰዎች፣ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ጠዋት፣ ቤቱን ለቀው እንዲወጡ የሦስት ቀናት ገደብ እንደሰጧቸው የተናገሩት ወይዘሮ ስንታየሁ ዓለማየሁ፣ ዛሬ ቤቱን እንዳሸጉባቸው አስታውቀዋል።
የመንግሥት የኪራይ ቤቶች አስተዳዳር፣ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ባይሰጥም፣ የሕግ ባለሞያ ግን፣ የመንግሥት ክራይ ቤት ውል እና ሕጎች እንዳሉት ገልጸዋል።
ባለፈው ሰኞ፣ በጸጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኀይል በቁጥጥር ሥር የዋሉት የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ደ’አታ አቶ ታየ ደንዳአ ባለቤት፣ እየኖሩበት ካሉት የመንግሥት ኪራይ ቤት፣ ዛሬ በጸጥታ ኃይሎች ለቀው እንዲወጡ መደረጋቸውን፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናገሩ።
በመኖሪያ ቤቱ፣ ላለፉት አራት ዓመታት፣ ከሁለት ልጆቻቸው እና በግጭት ምክንያት ከትውልድ ቀዬአቸው እንደተፈናቀሉ ከገለጿቸው ሌሎች የቤተሰብ አባላት ጋራ ሲኖሩበት እንደቆዩ የተናገሩት የአቶ ታየ ደንዳአ ባለቤት ወይዘሮ ስንታየሁ ዓለማየሁ፣ “ኹሉንም ዕቃችንን ሳናወጣ በጸጥታ ኀይሎች ታሽልጓል፤” ብለዋል።
ከኪራይ ቤቱ እንዲወጡ የሚያዘው የድርጅቱ ደብዳቤ፣ ትላንት ረቡዕ 10፡00 ላይ እንደደረሳቸው የገለጹት ወይዘሮ ስንታየሁ፣ ዛሬ ኀሙስ፣ ረፋድ 4፡00 ገደማ፣ የድርጅቱ ሓላፊዎች ከፖሊሶች ጋራ ወደ መኖሪያ ቤቱ በመምጣት አስገድደው እንዳስወጧቸው ተናግረዋል።
እርሳቸው የልጆች እናት እንደኾኑና ባለቤታቸው አቶ ታየም የምክር ቤት አባል እና ገና ተጠርጣሪ እንደኾኑ ገልጸው ሓላፊዎቹን ቢማፀኗቸውም፣ “ሊሰሙን አልቻሉም” ብለዋል ወይዘሮ ስንታየሁ። ለኪራይ ቤቶች አስተዳደር አቤቱታ ለማቅረብ ወደ መሥሪያ ቤቱ ቢሔዱም፣ የተከራይ አቤቱታ ረቡዕ ቀን ብቻ እንደሚያስተናግዱ እንደተገለጸላቸው ተናግረዋል።
SEE ALSO: አቶ ታየ ደንዳአ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ ባለቤታቸው ተናገሩከመኖሪያ ቤቱ ለቀው እንዲወጡ ከኪራይ ቤቶች የደረሳቸው ደብዳቤ፣ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ዕቃቸውን ካላወጡ፣ በራሳቸው ወጪ ወደ ሌላ መጋዘን ሊዛወር እንደሚችል ጭምር እንደሚያሳስብ፣ ወይዘሮ ስንታየሁ ጠቁመዋል።
የመኖሪያ ቤቱ፣ አቶ ታየ ደንዳአ የኦሮሚያ ክልል ፍትሕ ቢሮ ሓላፊ በነበሩ ጊዜ የተሰጣቸው እንደነበር የገለጹት ወይዘሮ ስንታየሁ፣ በወቅቱ እየኖረበት ለነበረው ሰው፣ በቂ የመፈለጊያ ጊዜ ተሰጥቶ እንደነበረ አስታውሰዋል።
በጉዳዩ ላይ፣ የመንግሥት ቤቶችን በበላይነት ከሚያስተዳድረው የመንግሥት ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።
በፌዴራል እና በኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች የሕግ አማካሪ እና ጠበቃ የኾኑት ዶክተር ናቶሊ ፈይሳ ግን፣ የአቶ ታየ ቤተሰቦች፣ በመንግሥት ከተሰጣቸው የኪራይ ቤት በአጭር ቀን ውስጥ እንዲወጡ መደረጋቸውን ተችተዋል፡፡
በፌዴራል፣ በዐዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የሚሠራባቸው የመንግሥት የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ሕግጋት የተለያዩ እንደኾኑ የገለጹት የሕግ ባለሞያው፣ ከተከራዩ ጋራ የሚደረግ ውልም ገዥ ይኾናል፤ ብለዋል። ይኹንና፣ አብዛኛዎቹ ሕጎች የማስጠንቀቂያ ጊዜ እንዳላቸው አመልክተዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሓላፊነታቸው ተነሥተው በቁጥጥር ሥር የዋሉት አቶ ታየ ደንዳአ፣ በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር እንደሚገኙ በትላንቱ ዘገባችን ላይ የተናገሩት ባለቤታቸው ወይዘሮ ስንታየሁ ዓለማየሁ፣ ስለተጠረጠሩበት ጉዳይ እና ቀጣይ የክስ ሒደት ዛሬም እንደማያውቁ አመልክተዋል።