ዩናይትድ ስቴትስ በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ የቀረበውን ጥያቄ በቪቶ ስልጣኗ አገደች 

አንቶኒዮ ጉተረዥ ሕዳር 28 2016

አንቶኒዮ ጉተረዥ ሕዳር 28 2016

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ ትላንት አርብ የእስራኤል ሀማስ ጦርነትን በተመለከተ በጸጥታው ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ካልተደረገ “መሰበሪያው ነጥብ ላይ ነን” በማለት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። ይሁን እንጂ ዩናይትድ ስቴትስ የጸጥታው ምክር ቤት ይኸን መሰል ጥያቄ እንዳያነሳ ድምጽን በድምጽ የመሻር የቪቶ መብቷን በመጠቀም አግዳለች።

ጉቴሬዥ “የጋዛ ሰዎች ወደ ገደሉ እየተመለከቱ ነው አለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ይኼንን መከራ ለማስቆም የሚችለውን ማድረግ አለበት” ብለዋል።

በጎርጎሮሳዊያን ጥቅምት ሰባት ሀማስ በእስራኤል ላይ በፈጸመው የሽብር ጥቃት 1,200 እስራኤላዊያን ሲሞቱ በሀማስ ቁጥጥር ስር በሚገኘው የጋዛ ሰርጥ እስራኤል እያደረገችው ባለው ጥቃት እስካሁን ድረስ ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ 17,000 ፍልስጤማውያን መሞታቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር መረጃ አስታውቋል። ከዚህ በተጨምሮም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በፍርስራሽ ተደብቀው የደረሱበት አልታወቀም።

ጉተሬዥ ረቡዕ እለት ለ15 የጸጥታው ምክር ቤት አባላት አንቀጽ 99 የተሰኘውን የመንግስታቱ ድርጅት ቻርተር በመጥቀስ ደብዳቤ የጻፉ ሲሆን አንቀጹ ለዋና ጸሀፊው የአለም አቀፍ ሰላምና ደህንነትን አደጋ ላይ ይጥላል ብሎ ያመኑትን ማንኛውንም ጉዳይ ለምክር ቤቱ እንዲያቀርቡ እና እንዲወስኑ ስልጣን የሚሰጥ ነው።

ጉተሬዥ በሰባት ዓመት የስልጣን ዘመናቸው ይሄንን አንቀጽ ለመጠቀም ጥሪ ሲያቀርቡ የመጀመሪያቸው ነው። ለመጨረሻ ጊዜ ይሄ አንቀጽ ስራ ላይ የዋለው እ.ኤ.አ በ1971 ባንግላዲሽ ከፓኪስታን በተገነጠለችበት ወቅት ነበር።

ጉተሬዥ የተኩስ አቁም ጥሪያቸው እንዲከበር ስልጣን የሚያጎናጽፋቸውን ይሄንን አንቀጽ ለመጠቀም ጥሪ ባቀረቡበት ወቅት የእስራኤሉ ልዑክ በዓለም ላይ የየመን እና የሶሪያ፣ እንዲሁም የዩክሬን ጦርነት የመሰሉ የኬሚካል የጦር መሳሪያዎች ሳይቀሩ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉባቸው ጦርነቶች ላይ ይሄን አንቀጽ ለመጠቀም እስካሁን ድረስ አልተሞከረም ሲሉ ተቃውመውታል። በአንጻሩ የፍልስጤሙ አቻቸው የምክርቤቱ አባላት ጥሪውን እንዲደግፉ “የጸጥታው ምክር ቤት ከ2.3 ሚሊየን በላይ ፍልስጤማውያንን ከማትረፍ የበለጠ ምን ጠቃሚ ጉዳይ አላቸው” ሲሉ ተማጽነዋል።

ይሁን እንጂ ውሳኔውን ዩናይትድ ስቴትስ ጥያቄን የቪቶ ስልጣኗን ያእደች ሲሆን ስታግደው ብሪታኒያ ድምጽ ከመስጠት ታቅባለች። ጥያቄውን ቀሪዎቹ 13 የምክር ቤት አባል ሀገራት የደገፉት ቢሆንም ሳይጸድቅ ቀርቷል። ሀማስ ዩናይትድ ስቴትስ የተረቀቀውን ስምምነት መቃወሟን ስነምግባር የጎደለው እና ኢ-ሰብዓዊ ሲል አውግዞታል።

ዩናይትድ ስቴትስ ለእስራኤል የቅርብ አጋር ስትሆን የተኩስ አቁም ለማድረግ ጊዜው አሁን አይደለም የሚል ግልጽ አቋሟን አስታውቃለች።