የመንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ድርድር በአስቸኳይ እንዲቀጥል በአሜሪካ የኦሮሞ ተቋማት ጠየቁ

  • ቪኦኤ ዜና

በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ የኦሮሞ ማኅበራት፣ የሃይማኖት እና የሲቪክ ተቋማት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ በአስቸኳይ ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመለሱ፣ ይህም ካልኾነ፣ ለሰብአዊ ርዳታ አፋጣኝ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲያደርጉ፣ ለሁለቱም አካላት በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ጠይቀዋል።

በመንግሥት እና በሠራዊቱ መካከል፣ ባለፈው ዓመት ግንቦት ላይ የተካሔደው የመጀመሪያ ዙር ድርድር ያለስምምነት ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ሁለተኛው ዙር ውይይት በታንዛኒያ - ዳሬ ሰላም መቀጠሉ አስደስቷቸው እንደነበር የገለጹት የኦሮሞ ተቋማቱ፣ በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ድጋፍ የተደረገለት ውይይት፣ ስምምነት ላይ ሳይደርስ መቋጨቱ እንዳሳዘናቸው አመልክተዋል።

“ሁለቱ ወገኖች ለስምምነት ቅርብ እንደነበሩ እናምናለን፤ ስምምነትም ሊኖር ይችላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤” ያለው የተቋማቱ መግለጫ፣ “የፖለቲካ ጥቅሞችን ወደ ጎን በመተው፣ በቅን ልቡና እንዲሁም የኦሮሚያን ሕዝብ ጥቅም በሚያራምድ መንገድ ከተደራደሩ፣ ጠመንጃን ዝም የሚያሰኝ ስምምነት ላይ ለመድረስ፣ እርቅ ለማውረድና ዘላቂ ሰላም ላይ ለመድረስ የሚያዳግታቸው ምንም ነገር የለም፤” ብሏል።

ሁለቱም ወገኖች የሚያስፈልጋቸው ወታደራዊ ድል በቀላሉ እንደማይደረስበት ማወቃቸው መሆኑን ገልጾ፣ በመጨረሻ ለድርድር ተቀምጦ መስማማቱ አይቀሬ እንደኾነ መገንዘብ እንደሚያስፈልግ፣ መግለጫው ጨምሮ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ማድረግ የሚችለውን አድርጎ፣ ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋራ መተማመንን ለመፍጠር የሚያስችሉትን በራስ መተማመንና አስፈላጊ የጸጥታ ግንባታ ርምጃዎች እንዲወስድ የኦሮሞ ተቋማቱ ጠይቀዋል፡፡ ታጣቂ ቡድኑም ኾነ መንግሥት፣ ግጭቱ ያደረሰውን የጥፋት መጠን ከግምት ውስጥ አስገብተው፣ በመከባበር እና በመርሕ ላይ የተመሠረተ ስምምነት ላይ እንዲደርሱም አሳስበዋል።

ተቋማቱ አክለውም፣ የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት(IGAD)፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረገው ድርድር ያለስምምነት ቢጠናቀቅም፣ ወደፊት ተጨማሪ ንግግሮች እንደሚኖሩ ተስፋ እንዳለው ማስታወቁና የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛም፣ በምክር ቤታቸው ቀርበው በሰጡት የምስክርነት ቃል፣ አሜሪካ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም እንዳላት መግለጻቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስም፣ የቀጣናው እና ዓለም አቀፍ አሸማጋዮች፣ እንዲሁም ታዛቢዎች፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል ዐዲስ ዙር ድርድር እንዲካሔድና ቀሪ ችግሮች ይፈቱ ዘንድ ድጋፍ ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉበት አሳስበዋል።