የእስራኤል ሐማስ የተኩስ አቁም ስድስተኛ ቀኑን ያዘ: እንዲራዘም እየተጠየቀ ነው

  • ቪኦኤ ዜና

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን

የእስራኤል እና የሐማስ መካከል የተኩስ አቁም ፋታ ዛሬ ረቡዕ ስድስተኛ ቀኑን አስቆጥሯል፡፡ ሁለቱ ወገኖች ተጨማሪ ታጋቾችን እና እስረኞችን እንደሚፈቱ ሲጠበቅ ተደራዳሪዎችም ተኩስ አቁሙ እንዲራዘም ግፊት ማድረጋቸው ተነግሯል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በዛሬ ረቡዕ ንግግራቸው “የተኩስ አቁሙ ፋታ እንዲራዘም እንፈልጋለን ከሁሉም በፊትና ከሁሉም በላይ ታጋቾቹ እንዲለቀቁ ወደ ቤታቸው ተመልሰው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንደገና እንዲቀላቀሉ ለማድረግ አስችሎናልና” ብለዋል፡፡ አያይዘውም “እንዲሁም ለጋዛ ህዝብ የምንሰጠውን እጅግ በጣም የሚያስፈልገውን የሰብአዊ ርዳታ እንድንጨምር አስችሎናል” በማለት ብለዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ብሊንከን ከእስራኤል እና ከፍልስጤም ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው ስለ እስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ፣ በጋዛ የዜጎችን ህይወት ስለመጠበቅ እና የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦትን ስለ ማፋጠን ጉዳይ ለመነጋገር ወደ ክልሉ እንደሚጓዙ ተነግሯል፡፡

በመጀመሪያው አራቱ ቀናት ሰብአዊ ተኩስ አቁም እስራኤል የሐማስን ተዋጊ ቡድን ለመደምሰስ የጀመረችውን ወታደራዊ ጥቃት እንድትገታ፤ ሐማስ እስራኤል ላይ ባደረሰው ጥቃት አእግቶ የወሰዳቸውን 50 ታጋቾች እንዲለቅቅ እና እስራኤል 150 ፍልስጥኤማውያን እስረኞችን እንድትለቅ እና ወደጋዛ ሰርጥ ተጨማሪ የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲገባ አስችሏል፡፡ በማስከተልም ሐማስ በቀን 10 ተጨማሪ ታጋቾችን፣ እስራኤልም ተጨማሪ እስረኞችን እንዲለቁ የሁለት ቀናት ተጨማሪ የሰብአዊ ተኩስ አቁም ስምምነት ተደርጓል፡፡

የእስራኤል የጦር ኅይል እንዳስታወቀው ጋዛ ውስጥ ታፍተው የነበሩ 10 እስራኤላውያን እና ሁለት የውጭ ሀገር ተወላጆች ትናንት ማክሰኞ አመሻሽ ወደእስራኤል ተወስደዋል፡፡ በአጸፋው እስራኤል 30 ፍልስጥኤማውያን እስረኞች ለቅቃለች፡፡ የተለቀቁት በዌስት ባንክ እና በእየሩሳሌም እስር ቤቶች የነበሩ 15 ሴቶች አና 15 ወጣት ወንዶች መሆናቸውን የፍልስጥኤማውያን እስረኞች ክበብ የተባለ ቡድን ተናግሯል፡፡

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ባደረሰችው የቦምብ ጥቃት፣ 2.3 ሚሊዮን ከሚሆነው የጋዛ ነዋሪ 1.8 ሚሊዮን የሚሆኑት በተጨናነቁ መጠለያዎች ውስጥ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አመልክቷል፡፡

በመንግስታቱ ድርጅት የሚመራው (Shelter Network, የተባለው) የእርዳታ ድርጅቶች ስብሰብ ባላፈው ዓርብ ባወጣው ዘገባ “ከ60 ከመቶ በላይ የሚሆነው የጋዛ ነዋሪ መኖሪያ ቤቶች ተጎድተዋል ወይም ወድመዋል” ብሏል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ትናንት ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ በተጨናነቀ ሁኔታ ውስጥ በምትገኘው ጋዛ የጤና ፣ የውሃ እና የንፅህና አጠባበቅ ስርዓት በመቋረጡ፣ ድንገተኛ የተላላፊ በሽታዎች ወረርሽኝ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቅቋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በእስራኤል እና በሐማስ ግጭት ላይ ያተኮረ ስብሰባውን ዛሬ ረቡዕ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡