ታጣቂዎች ከእስራኤል ጋር የተገናኘ ነዳጅ ጫኝ መርከብ የመን አቅራቢያ ያዙ

ዞዲያክ የባህር መርከብ ኩባንያ ይፋ ያደረገው፣ 'ሴንተራል ፓርክ' የተሰኘው ነዳጅ ጫኝ መርከብ

አጥቂዎች ከእስራኤል ጋር የተገናኘ የነዳጅ መርከብ የመን ውስጥ፣ በኤደን ባህር ዳርቻ ላይ መያዛቸውን ባለስልጣናት እሁድ እለት አስታወቁ። ለጥቃቱ እስካሁን ሀላፊነት የወሰደ ባይኖርም፣ ከቅርብ ቀናት ወዲህ የተፈፀሙት ቢያንስ ሁለት የባህር ላይ ጥቃቶች ከእስራኤል እና ከሐማስ ጦርነት ጋር ተያይዘው የመጡ ናቸው።

አጥቂዎቹ የላይቤሪያ ባንዲራ ሲያውለበልብ የነበረውን እና በኤደን ባህረሰላጤ የሚንቀሳቀሰው ዞዲያክ የባህር ኩባንያ የሚተዳደረውን መርከብ መያዛቸውን ኩባንያው እና አምብሬይ የተሰኘ የግል የስለላ ድርጅት አስታውቀዋል። አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ባለስልጣንም፣ ጥቃቱ መድረሱን ለአሶስዬትድ ፕሬስ አረጋግጠዋል።

ጥቃቱን ተከትሎ ዞዲያክ ባወጣው መግለጫ፣ "ቅድሚያ የምንሰጠው በመርከቡ ላይ ላሉት 22ቱ ሰራተኞቻችን ነው" ያለ ሲሆን፤ ቱርካዊ ካፒቴን የሚያሽከረክረው መርከብ ላይ፣ ከሩሲያ፣ ቬይትናም፣ ቡልጋሪያ፣ ህንድ፣ ጆርጂያ እና ፊሊፒንስ የመጡ ዜጎችን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ሰራተኞችን መያዙን አስታውቋል። መርከቡ ሙሉ ለሙሉ ፎስፈሪክ አሲድ መጫኑንም አመልክቷል።

ጥቃቱን ያደረሰው አካል ማን እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም። የኤደን ባህረሰላጤ፣ ዓለም አቀፍ እውቅና የተሰጠው የየመን መንግስት አጋር በሆኑ ኃይሎች እና፣ በኢራን ከሚደገፈው የሁቲ አማፂያን ጋር ለአመታት በተዋጋው ሳዑዲ መር ጥምረት ቁጥጥር ስር ሲሆን፣ ሁቲዎች ከሚቆጣጠሩት አካባቢውም የራቀ ነው። የሶማሊያ የባህር ላይ ዘራፊዎችም ከዚህ ቀደም በዛ አካባቢ ተንቀሳቅሰው አያውቁም።