በሴራሊዮን ታጣቂዎች ወታደራዊ ሰፈር ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን ተከትሎ ሰዓት እላፊ ታውጇል

አንድ የሴራሊዮን ጦር ዩኒፎርም የለበሰ ወታደር ጭር ባለው የፍሪታውን ጎዳና ላይ ለሚጓዝ ግለሰብ ሰላምታ ሲሰጥ ይታያል

በሴራሊዮን፣ ታጣቂዎች በዋና ከተማው ፍሪታውን የሚገኝ የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ፣ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት በመላ ሀገሪቱ የሰዓት እላፊ አውጀዋል። በምዕራብ አፍሪካ ቀጠና መፈንቅለ መንግስት በተስፋፋበት በዚህ ወቅት የደረሰው ይህ ጥቃት፣ በሀገሪቱ የስርዓት መፍረስ ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋትም ፈጥሯል።


የሴራሊዮን ፕሬዝዳንት ጁሊስ ማዳ፣ በኤክስ ወይም በቀድሞ አጠራሩ ትዊተር ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፣ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ፍሪታው በሚገኘው ዊልበርፎርስ የጦር ሰፈር ላይ በጠዋት ጥቃት ሰንዝረዋል ያሉ ሲሆን፣ ጥቃት አድራሾቹ በፀጥታ ኃይሎች መበተናቸውን እና ተመልሶ መረጋጋት መስፈኑንም አስታውቀዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለው፣ የጸጥታ ኃይሎች እየሸሹ ያሉትን ታጣቂዎች ከመሰረታቸው ማጥፋት እስኪችሉ በመላ ሀገሪቱ የሰዓት እላፊ መታወጁን ገልጸው፣ ዜጎች በተቻለ መጠን ከቤታቸው እንዳይወጡ አስጠንቅቀዋል።

የሀገሪቱ የማስታወቂያ እና ትምህርት ሚንስትር በበኩሉ ባወጣው መግለጫም፣ መንግስት እና የጸጥታ ኃይሎች ሁኔታውን መቆጣጠራቸውን በመግለፅ፣ ስምንት ሚሊየን የሚሆነው ህዝቧ ከዓለም ድሃ ተርታ በሚመደብባት ሀገር ውስጥ ሁከት እና ብጥብጥ ሊስፋፋ ይችላል የሚለውን ስጋት ለማስወገድ ሞክሯል።