የዝንጀሮ ፈንጣጣ ኮንጎ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በግብረ-ስጋ ግንኙነት መዛመቱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ

ምስሉ በማቀዝቀዣ ውስጥ የተቀመጡ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ክትባት ጠርሙሶችን ያሳያል

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ግዙፍ የተባለ ወረርሽኝ ጋር በመጋፈጥ ላይ ባለችበት በአሁኑ ሰዓት ፣ ፣ የዓለም የጤና ድርጅት የዝንጀሮ ፈንጣጣ በመባል የሚጠራው በሽታ ሀገሪቱ ውስጥ በግብረ ሥጋ ግንኙነት መተላለፉን ለመጀመሪያ ጊዜ አረጋግጫለሁ ሲል አስታውቋል ። ይሄም በሽታውን ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ሊያከብደው እንደሚችል የአፍሪካ ተመራማሪዎች አስታውቀዋል ።

የጤናው ድርጅት ሀሙስ ምሽቱን ባወጣው መግለጫ ፣ በመጋቢት ወር ወደ ኮንጎ ያቀና አንድ የቤልጂየም ዜጋ የዝንጀሮ ፈንጣጣ እንደተገኘበት ይፋ አድርጓል ። ግለሰቡ ፣ ከሌሎች ወንዶች ጋር የወሲብ ግንኙነት ያለው መሆኑን እንዲሁም ወደ ተለያዩ ድብቅ የተመሳሳይ ጾታ እና ከሁለቱም ጾታዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች መዝናኛ ስፍራዎችን ይሄድ እንደነበረ ድርጅቱ አስታውቋል ። ከግለሰቡ ጋር ግንኙት የነበራቸው 5 ሰዎች በሽታው እንደተገኘባቸው ድርጅቱ አክሏል ።

"ይህ በአፍሪካ የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የመተላለፉ የመጀመሪያው ትክክለኛ ማረጋገጫ ነው" ብለዋል - በተለያዩ የዓለም ጤና ድርጅት አማካሪ ቡድኖች ውስጥ አባል የሆኑት ናይጄሪያዊው ከቫይረስ ጋር የተገናኙ በሽታዎች አጥኚ ኦይዋሊ ቶሞሪ ። "ይህ ዓይነቱ ስርጭት እዚህ ሊከሰት አይችልም የሚለው ሀሳብ አሁን ውድቅ ሆኗል ።" ሲሉም አክለዋል ።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ (ኤምፖክስ ) በመካከለኛው እና ምዕራብ አፍሪካ ክፍሎች ለብዙ አሥርተ ዓመታት የተስፋፋ ሲሆን በአብዛኛው በበሽታው ከተያዙ አይጦች ወደ ሰዎች በመዛመት ውስን ወረርሽኞችን አስከትሏል።

ባለፈው ዓመት ፣ በዋነኝነት አውሮፓ ውስጥ ከተመሳሳይ ጾታ እንዲሁም ከሁለቱም ጾታዎች ጋር ግንኙነት ባላቸው ወንዶች ላይ የተከሰተው በሽታ ከ 100 በላይ አገሮችን አጥቅቷል። የዓለም ጤና ድርጅት ወረርሽኙን እንደ ዓለም አቀፍ ድንገተኛ አደጋ ያወጀ ሲሆን እስካሁንም ወደ 91,000 የሚጠጉ ሰዎች ላይ መከሰቱ ተነግሯል ።(ዘገባው የሶሼትድ ፕረስ ነው ።)