በሶማሊያ የጣለውን ከባድ ዝናም ተከትሎ በተከሰተው ጎርፍ ምክንያት፣ ከ30 በላይ ሰዎች ሞተዋል፣ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ቤታችውን ጥለው ለመውጣት ተገደዋል።
ኤል ኒኞ በተሰኘው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት፣ ሶማሊያ ውስጥ ላለፈው አንድ ወር የጣለው ከባድ ዝናም መኖሪያ ቤቶችን እና ማሳዎችን አጥለቅልቋል።
የጎርፍ አደጋው የመጣው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ረሃብ ጠርዝ ላይ ያስቀመጠውን ድርቅ ተከትሎ ነው።
በሰሞኑ ጎርፍ 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር ዳውድ አዊየስ አስታውቀዋል። የመንግሥት ባለሥልጣናት 31 ሰዎች ምሞታቸውን ቢያረጋግጡም፣ ቁጥሩ ከዛም ከፍ እንደሚል ሚኒስትሩ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የሸበሌ ወንዝ ከልክ በላይ በመሙላቱ በበለደወይን ከተማ የሚገኙ መንገዶችን እና ንብረቶችን አጥለቅልቋል። ባለፈው ግንቦት ወንዙ በመሙላቱ 200 ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ባለፈው ሳምንት እንዳስጠነቀቀው፣ ምናልባትም በመቶ ዓመት አንዴ በሚከሰተው ጎርፍ ምክንያት 1.6 ሚሊዮን ሰዎች ችግር ላይ ሊወድቁ ይችላሉ።