ሳዑዲ አረቢያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋራ የ533 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ልትፈራረም ነው

የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ሞሐመድ አል ጃዳን

የሳዑዲ አረቢያ የልማት ፈንድ፣ ከአፍሪካ ሀገራት ጋራ የ533ሚሊዮን ዶላር ስምምነት እንደሚፈራረም፣ የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ሞሐመድ አል ጃዳን፣ ሪያድ ላይ እየተካሔደ ባለው፣ የሳዑዲ አረቢያ እና የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮንፈረንስ ላይ ይፋ አድርገዋል።

ሚኒስትሩ አያይዘውም፣ ጋና እና ሌሎችም ሀገራት ያሉባቸውን ዕዳዎች አስመልክቶ፣ ከአጋሮቻቸው ጋራ እየሠሩ እንደኾነ ገልጸዋል።

700ቢሊዮን ዶላር የያዘው የአገሪቱ የልማት ፈንድ፣ በአፍሪካ ለውጥ የሚያመጣ ሙዓለ ነዋይ እንደሚያፈስ፣ የሳዑዲ የሙዓለ ነዋይ ሚኒስትር ኪአሊድ አል ፋሊህ፣ በኮንፈረንሱ ላይ አስታውቀዋል።

የአገሪቱ የኃይል ሚኒስትር ልዑል አብደላዚዝ ቢን ሳልማን፣ የኃይል ትብብርን የተመለከቱ ቅድመ ስምምነቶችን፥ ከናይጄሪያ፣ ከሴኔጋል፣ ከቻድ እና ከኢትዮጵያ ጋራ በኮንፈረንሱ ላይ እንደተፈራረሙም ታውቋል።

ለሆስፒታል እና የግድብ ግንባታ የሚውል የ158ሚሊዮን ዶላር ስምምነት፣ ከሳዑዲ የልማት ፈንድ ጋራ መፈራረማቸውን፣ የሞዛምቢኩ የገንዘብ ሚኒስቴር ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈ ወርቂ፣ በሪያዱ ኮንፈረንስ ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ታውቋል።