ሐማስ አምስት ታጋቾችን ለቀቀ

ፋይል - የጠፉ ወይም የታገቱ ሰዎች ፎቶ

የሐማስ ታጣቂ፣ ከአንድ ወር በፊት በእስራኤል በሰነዘረው ድንገተኛ ማጥቃት ወቅት፣ በቡድኑ ከታገቱት ከኻያ በላይ ሰዎች ውስጥ አምስቱን ትላንት እንደለቀቃቸው፣ የአሶሺዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።

የሌሎች ታጋቾች ቤተሰቦች ግን፣ የለቀቃ ሒደቱ ለምን ዘገምተኛ እንደኾነና አንዳንዶች ሲለቀቁ ሌሎች አለመለቀቃቸው ለምን እንደኾነ እየጠየቁ ይገኛሉ። በተጨማሪም ቤተ ሰዎቹ፣ እያየለ የመጣው የእስራኤል ጥቃት፣ የታጋቾቹን የመለቀቅ ተስፋ እንደሚያጨልም ስጋት አላቸው።

እስራኤል፣ ባለፈው ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ፣ አንድን ታጋች ነጻ እንዳወጣች አስታውቃ ነበር። እርሱም፣ የሠራዊት አባሉ ኦሪ ማጊዲሽ እንደኾነ ታውቋል።

ሐማስ፣ ከዚኽ ቀደም ሁለት አሜሪካውያን እናት እና ልጅን፣ እንዲሁም ሌሎች ሁለት በዕድሜ የገፉ ታጋቾችን ለቅቆ ነበር።

በእስራኤል የተያዙ በሺሕ የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን ከተለቀቁ፣ ሐማስ የያዛቸውን ታጋቾች በሙሉ እንደሚለቅ አስታውቋል። እስራኤል ግን፣ ይህን የሐማስን ቅድመ ኹኔታ እንደማትቀበል አስታውቃለች፡፡