በፓኪስታን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጋዛ የእስራኤልን የቦምብ ጥቃት በመቃወም ሰልፍ ወጡ

በሺዎች የሚቆጠሩ ፓኪስታናዊያን እስራኤል በጋዛ የምታካሂደውን የቦምብ ጥቃት ተቃውመው ሰልፍ ያካሄዱ ሲሆን ለፍልስጤማውያን ያላቸውን አጋርነት አሳይተዋል - ጥቅምት 18፣ 2016

በፓኪስታን ሀይማኖታዊ ፖለቲካ የሚያራምደው ፓርቲ ደጋፊ የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች፣ እስራኤል በጋዛ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ የምታደርሰውን ጥቃት በመቃወም በዋና ከተማው ኢስላማባድ እሁድ እለት ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል። ፀረ-አሜሪካ መፈክሮችን በማሰማትም ዩናይትድ ስቴትስ "አጥቂውን ትደግፋለች" በማለት ከሰዋል።

ፅንፈኛው ቀኝ ዘመም ፓርቲ ጃማአት-ኢ-ኢስላሚ የጠራው ሰልፍ በኢስላማባድ ከሚገኘው ዝንኛ አብፓራ አደባባይ ተነስቶ ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚደረግለት የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ እንዲያመራ ታስቦ ነበር። ሆኖም ባለስልጣናት ፓርቲው እቅዱን እንዲቀይር እና ሰላማዊ ሰልፉን ከኤምባሲው በራቀ ስፍራ ላይ እንዲያካሂድ አድርገውታል። ሴቶች እና ህፃናትን ጨምሮ የጃማአት-ኢ-ኢስላሚ ደጋፊዎች በርካታ ኪሎሜትሮችን ተጉዘው በሰልፉ ስፍራ ተገኝተዋል። እስራኤልን እና ዩናይትድ ስቴትስ የሚቃወሙ እና ፍልስጤማውያንን የሚደግፉ መፈክሮችንም አሰምተዋል።

"መድሃኒቶችን እና ጥቂት የእርዳታ ቁሳቁሶችን መላክ ብቻ በቂ አይደለም" ሲል የገለፀው የሰልፉ አስተባባሪ፣ የሙስሊሙ ዓለም መሪዎች ለጋዛ እንዲነሱ እና የአሜሪካ ባሪያ ከመሆን ይልቅ በአላህ ላይ እንዲመኩ አሳስቧል።

ጃማአት-ኢ-ኢስላሚ በጠራው ሰልፍ ምክንያት ሁከት ሊፈጠር ይችላል በሚል ስጋት የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ኢስላማባድ ውስጥ እና በአካባቢው የሚኖሩ የአሜሪካ ዜጎች "አላስፈላጊ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ" ማስጠንቀቂያ አውጥቷል። የአሜሪካ ዜጎች ህዝባዊ ስብሰባዎች ባሉባቸው አካባቢዎች እንዳይገኙም መክሯል።

ጀማአት-ኢ-ኢስላሚ ፍልስጤማውያን በመሬታቸው ነፃነታቸው እስኪያገኙ ድረስ ድምፁ ማሰማቱን እንደሚቀጥል አመልክቷል።