የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ሦስት አባላቱ ያለሕግ እንደታሰሩበት ገልጿል

Your browser doesn’t support HTML5

የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ሦስት አባላቱ ያለሕግ እንደታሰሩበት ገልጿል

በሲዳማ ክልል በሐዋሳ ከተማ እና በዞኖች አስተዳደር፣ ሰዎች ያለፍርድ ቤት መጥሪያ እየተያዙ እና እየታሰሩ እንደሚገኙ፣ የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ እና የታሳሪዎች ቤተሰቦች ለአሜሪካ ድምፅ ገለጹ።

የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ እንደገለጸው፣ ከተያዙት ግለሰቦች ሦስቱ የፓርቲው አባላት ሲኾኑ፣ የአንዳንዶቹም መኖሪያ ቤት፣ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደተበረበረ አመልክቷል፡፡

በቀጣይ እንዲያዙ የስም ዝርዝር ወጥቶባቸዋል የተባሉ 60 የክልሉ ነዋሪዎችም፣ ከአካባቢው እንደተሰወሩ፣ ፓርቲው አስታውቋል።

የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ በፌስ ቡክ ገጹ ባወጣው አጭር መግለጫ፣ የሲዳማ ብሔራዊ ክልል የጸጥታ ግብረ ኀይል፣ በመንግሥት እና በክልሉ ሕዝቦች መካከል ልዩነትን ለመፍጠርና ግጭትን ለማነሣሣት በስውር የሚንቀሳቀሱ አካላት እንዳሉና ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድባቸው መወሰኑን አስፍሯል።

የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ሊቀ መንበር እና የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ተሰማ ኤልያስ፣ ክልሉ ይህን ያደረገው፣ አሉበት የሚባለውን፥ የሌብነት፣ የሥርዐት አልበኝነት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳይጋለጡበት ነው፤ ሲሉ ተችተዋል።

የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ሓላፊ አቶ ኢያሱ ዳዊት በበኩላቸው፣ “ለግል ጥቅም ሥልጣን የሚሹ ግለሰቦች የሚነዙት ሐሰት ነው፤” ሲሉ፣ ትችቱን አጣጥለዋል።

ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።