የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ መንግስት ሀገሪቱን ለማተራመስ ትናንት ረቡዕ የተሞከረውን መፈንቅለ መንግስት የደህንነትና የጸጥታ ተቋማት ማክሸፋቸውን አስታወቀ።
ወታደራዊው መንግሥቱ ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ተካሄዷል ስላለው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ዝርዝር አልገለጸም፡፡
የመፈንቅለ መንግሥቱ መክሸፍ ዜና የወጣው የሀገሪቱ ዜጎች ወደ ዋና ከተማይቱ ዋጋዱጉ ጎዳናዎች በመውጣት ለአሁኑ የሽግግር መንግስት ድጋፋቸውን ከሰጡ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
የወታደራዊ መንግሥቱ ቃል አቀባይ ሪምታልባ ዣን ኢማኑኤል ኦውድራጎ “በርካታ መኮንኖችና በተፈጠረው የማተራመስ ሙከራ ውስጥ ተሳትፈዋል የተባሉት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እንዲሁም ሌሎችም እየታደኑ” መሆኑን በጽሁፍ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ይህ የቡርኪና ፋሶን ያልተረጋጋ የአስተዳደር ሁኔታ አጉልቶ የሚያሳይ ሲሆን ሀገሪቱ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ መንግስታት በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ከተወገዱባቸው የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ውስጥ አንዷ ናት።
በቡርኪናፋሶ በቀጠለው ሁከት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ2 ሚሊዮን በላይ መፈናቀላቸው እና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት በረሃብ አፋፍ ላይ መሆናቸውን የአሶሴይትድ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል፡፡