ኢትዮጵያ፣ የታላቁ የሕዳሴ ግድብን አራተኛ ሙሌት እንዳጠናቀቀች ስታስታውቅ፣ ግብጽ በበኩሏ፣ “ሕገ ወጥ ነው” ስትል አወገዘች፡፡
ሚኒስቴሩ፣ ትላንት እሑድ፣ ጳጉሜን 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ዐዲስ አበባ፣ የግድቡን ሙሌት ለማጠናቀቅ የወሰደችው “የተናጠል” ውሳኔ፣ “እ.ኤ.አ በ2021 ዓ.ም ተቋርጦ ባለፈው ወር ዳግም የተጀመረውን የሦስትዮሽ ድርድር ወደ ጎን የተወ ነው፤” ማለቱን አሶሺዬትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ “በውስጥ ፈተና፣ በውጭ ጫና ነበረብን። ከፈጣሪ ጋራ የመጣውን ሁሉ ተቋቁመን ለዚኽ ደርሰናል፤” ሲሉ፣ የሕዳሴ ግድቡ አራተኛ ሙሌት እንደተጠናቀቀ፣ ትላንት እሑድ፣ በፌስቡክ የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በካርቱም በሦስቱ ሀገራት የተፈረመው የ2015 የመርሖዎች ስምምነት፣ ሦስቱ ሀገራት፥ በሕዳሴ ግድቡ ሙሌት እና የመተዳደሪያ ደንቦች ላይ መስማማት እንዳለባቸው የደነገገውን አስታውሷል፡፡
አያይዞም፣ “የኢትዮጵያ የአንድ ወገን አካሔድ፣ በዓለም አቀፍ ሕግ የተደነገጉ የተፋሰሱን የታችኛው ሀገራት መብት እና ጥቅም፣ እንዲሁም የውኃ ደኅንነታቸውን ወደ ጎን የተወ ነው፤” ሲልም ተችቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከግብጽ በኩል ስለቀረበው ወቀሳ እስከ አሁን በይፋ የሰጠው ምላሽ የለም፡፡
ኾኖም፣ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን መሪና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ(ዶር.)፣ ባለፉት አራት ዓመታት፣ የውኃ ሙሌት ሥራውን ለማከናወን የሚያስችል በቂ የዝናም መጠን እንደተገኘና በታችኛው ተፋሰስ ሀገራትም ላይ ምንም ዐይነት ጉዳት በማያደርስ መልኩ እንደተከናወነ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የግድቡ የውኃ ሙሌት፣ ከግንባታው ሒደት ጋራ ጎን ለጎን እንደሚከናወን የምትገልጸው ኢትዮጵያ፣ ይህም፣ ሦስቱ ሀገራት በተፈራረሙት የመርሖዎች ስምምነት መሠረት እንደሚፈጸም በተደጋጋሚ አስታውቃለች፡፡
በአፍሪካ ኅብረት አመቻችነት የሚካሔደው የሦስትዮሽ ድርድር፣ እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 2021 ከተቋረጠ በኋላ፣ በነሐሴ ወር በካይሮ አስተናጋጅነት የተካሔደው ውይይትም፣ ተጨባጭ ውጤት እንዳላመጣ ግብጽ ይፋ አድርጋለች፡፡ ለዚኽም “ግትር አቋም ይዛለች፤” ያለቻትን ኢትዮጵያን ተጠያቂ አድርጋለች፡፡
ባለፈው ሳምንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ስለ ግብጽ ወቀሳ እና ትችት ጥያቄ የተነሣላቸው፣ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም፣ ውድቅ አድርገውታል፡፡
ኢትዮጵያ፣ በግድቡ ጉዳይ ሦስቱንም ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ላይ ለመድረስ ዝግጁ እንደኾነች የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ በካይሮው ውይይት ላይ፣ “ግብጽስ ከቀድሞው የተለየ ምን አቋም አራምዳለች?” በሚል መጠየቅ እንዳለባት አመልክተዋል፡፡
በአወዛጋቢው የሕዳሴ ግድብ ውኃ ሙሌት ጉዳይ፣ ቀጣይ ዙር የሦስትዮሽ ውይይት፣ በዐዲስ አበባ እንደሚካሔድ ይጠበቃል፡፡