የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፣ የአፍሪካ ህብረት፣ ቡድን 20 በመባል የሚታወቁትን የዓለም ከፍተኛ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራት ስብስብን እንደሚቀላቀል ዛሬ ቅዳሜ ባደረጉት ንግግር አስታወቁ። ሞዲ አክለው፣ የህብረቱ ቡድኑን መቀላቀል፣ ዓመታዊውን ጉባዔ ሀገራቸው እያስተናገደች ባለችበት ወቅት ዝቅተኛ ኢኮኖሚ እና የኢንዱስትሪ ልማት ያላቸው ሀገራት ድምፃቸው እንዲሰማ የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚያበተታታው አመልክተዋል።
ሞዲ ዛሬ በተጀመረው፣ የቡድን 20 የሁለት ቀን ጉባዔ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ይፋ ያደረጉት ውሳኔ የተላለፈው በዓለም ዙሪያ ያለው መከፋፈል እና የቁልፍ ተዋንያን አለመኖር፣ አሳሳቢ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነት ላይ ለመድረስ አዳጋች እየሆነ በመጣበት ወቅት መሆኑ ተገልጿል።
የአፍሪካ ህብረት፣ ከአውሮፓ ህብረት ቀጥሎ ሁለተኛው ቀጠናዊ ቡድን በመሆን፣ ቡድን 20ን እንዲቀላቀል ሰፊ ድጋፍ ሲደረግ ቆይቷል። ሞዲ ውሳኔውን ካሳወቁ በኃላ፣ ከአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የኮሞሮስ ፕሬዝዳንት አዛሊ አሱማኒ ጋር በመጨባበጥ እና በመተቃቀፍ ደስታቸውን የገለፁ ሲሆን፣ ሞቅ ባለ ሁኔታ ጠረጴዛው ላይ እንዲቀመጡ ጋብዘዋቸዋል።
ግሎባል ሳውዝ በመባል ለሚታወቁት ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራት ድምፅ መስጠት መቻል የዚህ ዓመቱ ጉባዔ ዋና አካል መሆኑን የገለፁት ሞዲ፣ በስፍራው የተሰበሰቡት መሪዎች፣ ሽብርኝነትን፣ የሳይበር ደህንነት፣ ጤና እና የውሃ ደህንነትችን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ለሚታዩት ውጣ ውረዶች እና ሰፊ ተግዳሮቶች "ተጨባጭ መፍትሄ" እንዲያገኙ አሳስበዋል።
በኒው ደልሂ ዛሬ በተጀመረው የቡድን 20 ጉባዔ ላይ ቢያንስ አንድ አምስተኛ የሚሆኑት መሪዎች አልተገኙም። የሩሲያ እና የቻይና መሪዎች፣ በተለይ የዩክሬን ጦርነትን ጨምሮ፣ ከአሜሪካ እና አውሮፓ አቻቸው ጋር ባሉባቸው በርካታ አለመግባባቶች ዙሪያ ፊት ለፊት ላለመነጋገር፣ በስበሰባው ላለመገኘት መርጠዋል። የስፔን ፕሬዝዳንት በኮቪድ 19 በመያዛቸው ምክንያት መገኘት ያልቻሉ ሲሆን፣ የሜክሲኮ ፕሬዝዳንትም በጉባዔው እንደማይገኙ አስታውቀዋል።