“እስራኤል የዘር መድልዖ ታካሂዳለች” - የቀድሞ ሞሳድ አለቃ

ፎቶ ፋይል፦ የቀድሞው የሞሳድ አለቃ ታሚር ፓርዶ

እስራኤል በዌስት ባንክ በሚገኙ ፍልስጤሞች ላይ የዘር መድልዖ (አፓርታይድ) ሥርዓትን በመከተል ላይ ነች ሲሉ አንድ የቀድሞው የእስራኤል የስለላ ተቋም (ሞሳድ) አለቃ ለአሶስዬትድ ፕረስ ተናግረዋል።

የቀድሞው የሞሳድ አለቃ ታሚር ፓርዶ፣ በጉዳዩ ላይ ተመሳሳይ አቋም ያላቸውንና ጡረታ የወጡ የእስራኤል ባለሥልጣናት ተቀላቅለዋል።

እስራኤል ፍልስጤማውያንን የያዘችበት መንገድ እንደ አፓርታይድ ይቆጠራል ሲሉ በርካታ የቀድሞ የእስራኤል ባለሥልጣናት በመናገር ላይ ናቸው።

“በአንድ ግዛት ውስጥ ያሉ ሰዎች በሁለት ሕግ የሚዳኙ ከሆነ፣ የአፓርታይድ ሥርዓት ነው” ሲሉ ተናግረዋል ታሚር ፓርዶ።

እስራኤል ለ 56 ዓመታት በያዘችው ዌስት ባንክ ፍልስጤማውያንን እንደ ሁለታኛ ደረጃ ዜጋ በመቁጠር፣ የአይሁዳችን የበላይነት ከጆርዳን ወንዝ እስከ ሜዲትሬንያን ባህር ለማስጠበቅ እየሰራች ነው ሲሉ በእስራኤል እና በውጪ የሚገኙ የመብት ተሟጋቾች እና ፍልስጤማውያን ይከሳሉ።

የቀድሞ የእስራኤል መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች እና የጸጥታ ኃላፊዎች እስራኤል የዘር መድልዖ የሰፈነባት ሀገር እንዳትሆን በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው።

እስራኤል የዘር መድልዖ አለ የሚለውን ክስ አስተባባላ፣ የአረብ ዜጎቿ እኩል መብት እንዳላቸው ትገልጻለች፡፡ ዌስት ባንክም አጨቃጫቂ ግዛት በመሆኑ፣ ዕጣ ፈንታው በድርድር መወሰን አለበት ትላለች፡፡