እስራኤል ኤርትራውያንን በጅምላ ከማባረር እንድትቆጠብ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠይቋል። የእስራኤል ባለሥልጣናት በዛቱት መሠረት ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከሀገሪቱ የሚያስወጡ ከሆነ፣ “ዓለም አቀፍ ሕግን እንደሚተላለፉ” እና ከፍተኛ ሰብዓዊ ችግር እንደሚያስከትልም ድርጅቱ አስታውቋል።
በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች እና በተቃዋሚዎች መካከል፣ ባለፈው ቅዳሜ በቴል አቪቭ - እስራኤል በተፈጠረ ግጭት፣ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች መጎዳታቸውንና ንብረት መውደሙን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ባለሥልጣናት፣ በግጭቱ የተሳተፉ ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከሀገር እንደሚያስወጧቸው ዝተው ነበር፡፡
የኤርትራን 30ኛ ዓመት የነፃነት ቀን አስመልክቶ፣ በቴል አቪቭ ተዘጋጅቶ በነበረ ክብረ በዓል ላይ፣ የኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች በአንድ ወገንና ተቃዋሚዎች በሌላ ወገን ተሰልፈው በተፈጠረ ኀይል የተቀላቀለበት ግጭት ዐያሌዎች ተጎድተዋል። የፖሊስ አባላትም ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
የተፈጠረው ግጭት እጅግ እንዳሳሰበው የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ገልጾ፣ መረጋጋት እንዲኖር እና ሁለቱም ወገኖች ሁኔታውን ከማባባስ እንዲቆጠቡ ጠይቋል።
ባለፈው ሰኔ በወጣ መረጃ፣ 17 ሺሕ 850 ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች በእስራኤል እንደሚገኙ ታውቋል።
በግጭቱ 170 ጥገኝነት ጠያቂዎች እና በደርዘን የሚቆጠሩ የእስራኤል ፖሊስ አባላት እንደተጎዱ የስደተኞች ኮሚሽኑ ገልጿል።