የማዕከላዊ አፍሪካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ጋቦንን ከዓባልነት አገደ

  • ቪኦኤ ዜና
የሪፐብሊካን የጥበቃ ወታደሮች፣ በሊብራቪል መንገድ ላይ በታጠቁ መኪናቸው ላይ ሆነው ይታያሉ ነሐሴ 30, 2023.

የሪፐብሊካን የጥበቃ ወታደሮች፣ በሊብራቪል መንገድ ላይ በታጠቁ መኪናቸው ላይ ሆነው ይታያሉ ነሐሴ 30, 2023.

የማዕከላዊ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢካስ) ኢኳቶሪያል ጊኒ ላይ ባደረገው ልዮ ጉባኤ ጋቦንን ከአባልነት አግዶ፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን በኃይል ለመፍታት የሚደረግ ጥረትን አውግዟል።

በጋቦን አሊ ቦንጎ በመፈቅለ መንግስት ከተወገዱ ወዲህ፣ በመጀመሪያው ቀን በለቀቁት የቪዲዮ መልዕክት ዓለም አቀፍ እገዛ ከጠየቁ ወዲህ አልታዩም።

ጋቦን ወደ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት እንድትመለስና በሀገሪቱ የሚገኙ ተቋማት መልሰው እንዲከፈቱ የኢኮኖሚ ማሕበረሰቡ ጠይቋል።

ሆኖም ሕገ መንግስታዊ ባልሆነ መንገድ ሥልጣን በመነጠቁ፣ ጋቦን ከኢኮኖሚ ማኅበረሰቡ መታገዷን ኢካስ አስታውቋል።

ከአምስት ቀናት በፊት ወታደራዊ ኦፊሰሮች በብሔራዊ ቴሌቭዥን ቀርበው ሥልጣኑን መቆጣጠራቸውን አስታውቀው፣ ፕሬዝደንት አሊ ቦንጎን በቁም እሥር አውለዋቸዋል። ልጃቸው ኑረዲን ቫለንቲንም በሃገር ክህደት ተወንጅለው በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የሁንታው መሪ፣ ጀኔራል ብሪስ ንግዌማ ትናንት ሰኞ ግዜያዊ ፕሬዝደንት በመሆን ቃለ መሃላ ፈፅመዋል። ሥልጣኑን በሲቪል ለሚምራ መንግስት እንደሚያስተላልፉ የተናገሩት ንግዌማ መቼ እንደሚፈጸም ያሉት ነገር ባይኖርም፣ ለምርጫ እንደማይቸኩሉ ግን አመልክተዋል።