የኖቤል ፋውንዴሽን የሩሲያ፣ የቤላሩስ እና የኢራን ተወካዮች በዚህ ዓመት የኖቤል ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ እንዲገኙ ያቀረበውን ግብዣ መሰረዙን በዛሬው ዕለት አስታውቋል ።የአሁኑ ውሳኔ የተሰማው የቀደመው አጨቃጫቂ ውሳኔ ጠንካራ ምላሾችን ካስተናገደ በኃላ ነው ።
የላቀ ክብር የሚሰጠውን ሽልማት የሚያስተዳድረው የግል ተቋም ከዓመት በፊት የነበረውን አቋም በመቀየር ለሦስቱ አገሮች ተወካዮች ግብዣ መላኩን ተከትሎ ፣ በርካታ የስዊድን የሕግ አውጭዎች በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም የሚካሄደውን የዘንድሮውን የኖቤል ሽልማት ሥነ-ሥርዓት እንደማይካፈሉ ተናግረዋል ።
አንዳንድ የህግ አውጭዎች ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ጦርነት እና የኢራን የሰብአዊ መብት ረገጣን ለተቃውሞቸው በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ኡልፍ ክሪስተርሰን አርብ ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት ፣ ምርጫ ካላቸው በዚህ አመት የሩሲያ ተወካዮች በክብረ በዓሉ ላይ እንዲገኙ እንደማይፈቅዱ አስታውቀዋል ።
የኖቤል ፋውንዴሽን ባሰራጨው አጭር መግለጫ የኖቤል ሽልማት የሚወክላቸውን እሴቶች እና መልእክቶች በተቻለ መጠን በስፋት መድረስ አስፈላጊ እና ትክክል ነው ብሎ ማመኑ የውሳኔው መሰረት እንደሆነ አስታውቋል ።
ሆኖም ግን ነባሩን ልምድ በመከተል ሁሉም አምባሳደሮች በኦስሎ የኖቤል የሰላም ሽልማት በሚሰጥበት ስነ ስርዓት ላይ እንዲገኙ እንደሚጋብዝ አስታውቋል።
የኖቤል ፋውንዴሽን ቀደም ሲል በስዊድን እና ኖርዌይ ውስጥ ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ ላላቸው ሁሉም ሀገራት ታህሳስ 10 ቀን ለሚከናወነው ዝግጅት ግብዣ ማቅረቡን ተናግሯል ።