ተቋርጦ የነበረው እና ከዩክሬን ወደ ተቀረው ዓለም ይወጣ የነበረው እህል መልሶ እንዲቀጥል ለማስቻል፣ ሩሲያ ለጥያቄዎቿ መልስ እንደምታገኝ ምንም ፍንጭ አይታይም ሲሉ፣ የሀገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ዛሬ ተናግረዋል።
የምዕራቡ ዓለም የጣለባት ማዕቀብ የራሷን እህልና ማዳበሪያ ለዓለም ገበያ ማቅረብ እንዳትችል አድርጓል በሚል፣ በጥቁር ባህር በኩል እህል ከዩክሬን ለተቀረው ዓለም እንዲደርስ ሲያደርግ ከቆየው ስምምነት ሩሲያ ባለፈው ሐምሌ ወጥታለች፡፡
የጥቁር ባህሩን ስምምነት ካደራደረችው የቱርክ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ላቭሮቭ፣ “ጥያቄዎቿ ከተመለሱ፣ ሩሲያ ወደ ስምምነቱ ነገ መመለስ ትሻለች፣ ነገር ግን ያ እንደሚሆን የሚታይ ምልክት የለም” ሲሉ ተናግረዋል።
የቱርኩ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን በበኩላቸው፣ “ሩሲያ የራሷን እህል እና ማዳበሪያ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ጠይቃለች፣ ጥያቄውም ተገቢ ነው፣ ይህን ጥያቄ መመለስ አስፈላጊ መሆኑንን እናምንበታለን” ብለዋል።
በቱርክ ረዳትነት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አዲስ ሃሳብ ይዞ መቅረቡን እና ይህም እህል መልሶ ከዩክሬን ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ያስችላል የሚል እምነት እንዳላቸው የቱርኩ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጨምረው ተናግረዋል።
ላቭሮቭ በበኩላቸው፣ ችግሩ መፍትሄ እንዳያገኝ የምዕራቡ ዓለም እንቅፋት ሆኗል ሲሉ ከሰዋል።