በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪቃ ያለውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለመዋጋት ያላቸውን አቅም አስተባብረው እንደሚሰሩ የተለያዩ የመንግስታቱ ድርጅት ተቋማት በጋራ አስታወቁ።
ትላንት ሰኞ ካይሮ ላይ ይፋ ያደረጉት ይህ ውጥን ድርጅቶቹ በተናጠል ያሏቸውን ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ አቅሞች በማዋሃድ የሕፃናትን የሰውነት መሟሸሽ እና ለበሽታ አጋላጭ የሆነ ከመጠን በላይ ውፍረት የመሳሰሉ ችግሮች በተሻለ መዋጋት እንደሚያስችላቸው አመልክተዋል።
“በሜና ግዛት ውስጥ ብቻ ቁጥራቸው 10 ሚሊዮን የሚደርስ ህጻናት ለእድገት መቀጨጭ ተጋልጠዋል። 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ያህሉ ለሕይወት አስጊ ለሆነ የሰውነት መሟሸሽ ሲጋለጡ፤ ሌሎች ቁጥራቸው አምስት ሚልዮን የሚጠጋ ህፃናት ደግሞ ከመጠን ላለፈ ውፍረት ተዳርገዋል” ሲሉ የዓለም አቀፉ የህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ የመካከለኛው ምስራቅ እና የሰሜን አፍሪቃ ክልላዊ ዳይሬክተር አዴሌ ኮድር አስረድተዋል።
በተባበሩት መንግስታት ሪፖርት መሰረት፣ በእነኚህ አገሮች ውስጥ ከሚኖሩት ህፃናት 15 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆኑት ስር የሰደደ የምግብ እጥረት ለሚያስከትላቸው የተለያዩ ችግሮች ተጋልጠዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ የተባበሩት መንግስታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እና እንዲሁም የመንግስታቱ ድርጅት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) ናቸው ለተደራረቡ ችግሮች የተጋለጡት ሕፃናት የገጠማቸውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ፈተና ለመቅረፍ አቅማቸውን ለማስተባበር እና በጋራ ለመስራት መወሰናቸውን ይፋ ያደረጉት።
አካባቢው ህጻናት ለአስከፊ ረሃብ እና ለሌሎች ብርቱ ችግሮች የተጋለጡበት በጦርነት የተበታተኩ በርካታ ሃገሮች የሚገኙበት ሲሆን፤
እንደ ዓለሙ የምግብ ፕሮግራም ዘገባም በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ ለረሃብ የተጋለጠው አጠቃላይ ህዝብ ቁጥር 345 ሚሊዮን ድርሷል።