ፈረንሳይ ትምሕርት ቤቶች ውስጥ የሙስሊም ረዥም ቀሚሶች እንዳይለበሱ አገደች

ፋይል - በፓሪስ የሚገኝ አንድ መስጊድ

ፈረንሳይ አንዳንድ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ ሴቶች የሚለብሱትን ‘አባያ’ የተባለ በረዥሙ የሚለቀቅ የቀሚስ ዓይነት ሕጻናት በመንግስት ትምሕርት ቤቶች ውስጥ እንዳይለብሱ አገደች።

የፈረንሳይ ትምሕርት ሚኒስቴር ትምህርት ቤቶች ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ከመከፈታቸው አስቀድሞ ባወጣው መግለጫ ነው እገዳውን ይፋ ያደረገው።

እገዳው ትላንት ሰኞ ፓሪስ ውስጥ ከአንዳንዶች ዘንድ አድናቆት ሲቸረው፤ ከሌሎች ዘንድ ደግሞ ትችት የተንጸባረቀባቸውን የተለያዩ አስተያየቶች አስተናግዷል።

ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንስቶ ባሕላዊ የካቶሊክ ኃይማኖት ተፅእኖዎችን ከሕዝብ ትምህርት ቤቶች በማስወገድ፡ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ምልክቶች በመንግስት ትምሕርት ቤቶች ውስጥ እንዳይደረጉ ጥብቅ እገዳ የጣለችው ፈረንሳይ፤ ቁጥሩ እየጨመረ የመጣውን ሕዳጣን የሙስሊም ማሕበረሰብ አባላት ተጽዕኖ ለመቋቋም በሚያስችል መልኩ የቀደሙ መመሪያዎቿን ለማሻሻል ስትታግል ቆይታለች።

ፈረንሳይ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2004 ጽጉር የሚሸፍኑ ልብሶች ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዳይለበሱ ስትከለክል፤ በ2010 ሙሉ ፊት የሚሸፍኑ ልብሶች በአደባባይ እንዳይደረጉ የሚያዝ እገዳ ባወጣችበት ወቅት፡ እርምጃው ቁጥሩ አምስት ሚሊዮን የሚደርሰውን የሙስሊም ማህበረሰብ አባል ማስቆጣቱ ይታወሳል።

ሃይማኖታዊ ተጽዕኖዎችን መከላከል ፈረንሳይ ውስጥ የግለሰብ ነፃነት እሴት ከሚያቀነቅኑት ግራ ዘመም የፖለቲካ አራማጆች፣ በዚያች አገር እያደር እያደገ የመጣው የእስልምና ዕምነት ያለውን ሚና እስከሚቃወሙት ቀኝ ዘመም የፖለቲካ አራማጆች ድረስ የተለያየ የፖለቲካ አስተሳሰብ ከሚከተሉ ወገኖች ዘንድ የሚስተጋባ እና ሰፊ ቅቡልነት ያለው ዝንባሌ ነው።